ጾሙ ምዕመናን ከጥላቻ ፣ ፍትሕን ከማጉደል፣ ከበደልና ከዛቻ የሚቆጠቡበት ሊሆን ይገባል - ብጹዕ አቡነ ማቲያስ

102
አዲስ አበባ የካቲት 15/2012 ( ኢዜአ) በመጪው ወርሃ ጾም ምዕመናን ከጥላቻ ፣ ፍትሕን ከማጉደል፣ ሰውን ከመበደልና ከዛቻ እንዲቆጠቡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን አሳሰበች። የቤተክርስቲያኗ ፓትርያርክ ብጹዕ አቡነ ማቲያስ ነገ በመላው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እምነት ተከታዮች ዘንድ የሚጀመረውን የአብይ ጾም አስመልክቶ የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት አስተላልፈዋል፡፡ ፓትርያርኩ በዚሁ መልዕክታቸው እንዳስገነዘቡት፤ ሕዝበ ክርስቲያኑ ወርሃ ጾሙን ከቂምና ከበቀል ርቆ በመልካም ስነ ምግባርና በመንፈሳዊ ሕይወት አሸብርቆ ሊያሳልፍ ይገባዋል። ''በዚህ ወቅት ማዳመጥ ያለብን የፈጣሪን ድምጽ ብቻ ነው'' ያሉት አቡነ ማትያስ፤ ''የፈጣሪ ድምጽ ደግሞ ፍቅርና ሰላም፣ አንድነትና ስምምነት፣ እርቅና ይቅርታ ምሕረትና ቸርነት፣ ርሕራሔና ሀዘኔታ፣ ጸሎትና ምጽዋት፣ ፍትሕና እውነት እንዲሁም እኩልነትና ሕብረት ናቸው'' ብለዋል። ኢትዮጵያ አሁን የገጠማትን ችግር በጾምና በጸሎት ከመትጋት የተሻለ አማራጭ እንደሌለ አመልክተዋል። ጾም ሲባል ወደ ሰዎች አእምሮ የሚመጣው የእንስሳት ውጤት ከሆኑ ምግቦች መከልከልና ሰዓት ጠብቆ መመገብ እንደሆነ ያመለከቱት አቡነ ማቲያስ፤ ጾም በንስሐ ወደ እግዚአብሔር መቅረብም መሆኑን መገንዘብ እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል። ''ወደ ፈጣሪ ስንቀርብ በፍጹም ሐሳባችን፣ በፍጹም ልባችን በፍጹም ነፍሳችን ነውና በአካላችንና በመንፈሳችን ሁሉ ለእግዚአብሔር ሙሉ በሙሉ ለመታዘዝ ዝግጁ በመሆን ነው'' ሲሉም አስገንዝበዋል። ምዕመናን ጾም ለእግዚአብሔር እንዲታዘዙ የሚያደርግ ፍቱን መሳሪያ በመሆኑ ወደ ፈጣሪ ቀርበው ለመለመንና ለመስማት እንዲሁም ንስሐ እንዲገቡም ፓትርያርኩ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም