በጋምቤላ ክልል ማጃንግ ዞን የቡና ምርት መቀነሱ ተገለፀ

108
ጋምቤላ (ኢዜአ) የካቲት 15 /2012 ዓ.ም በጋምቤላ ክልል ማጃንግ ዞን በዘንደሮው ዓመት የተሰበሰበው የቡና ምርት መጠን ወቅቱ ባልጠበቀ ዝናብና በሰራተኞች እጥረት ምክንያት መቀነሱን የዞኑ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ቢሮ ገለፀ ። ቢሮው እንደገለፀው በክልሉ ማጃንግ ዞን በዘንድሮው ዓመት 371 ሺህ 200 ኩንታል የታጠበና ቅሽር የቡና ምርት ተገኝቷል ። በምርት ዘመኑ የቡና ማሳቸው የተሻለ ምርት ይዞ የነበረ ቢሆንም በሰራተኛ እጦትና ወቅቱን ባልጠበቀ ዝናብ ምክንያት ለብልሽት እንደተዳረገባቸው የዞኑ አርሶ አደሮች ገልጸዋል። በክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሃብት ቢሮ የቡና፣ ሻይና ቅመማ ቅመም ምርት ጥራት ዳይሬክተር አቶ እሸቱ ዘውዴ እንዳሉት ምርቱ የተገኘው በዞኑ በሚገኙ የጎደሬና የመንጌሽ ወረዳዎች በአርሶ አደሮችና በባለሀብቶች ከለማው 41 ሺህ 780 ሄክታር የቡና ማሳ ነው። በምርት ዘመኑ ካለፈው ዓመት የተሻለ ምርት እንደሚገኝ ተጠብቆ የነበረ ቢሆንም በለቀማ ወቅት ባጋጠመ የሰራተኛ እጥረትና በነበረው ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ የምርት ብክነት ማጋጠሙን ተናግረዋል። በዚህም ምክንያት በምርት ዘመኑ የተገኘው የቡና ምርት መጠን ካለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር በ14 ሺህ ኩንታል እንዲቀንስ አድርጎታል ብለዋል። የተገኘው ምርት በተሻለ ዋጋ እንዲሸጥ የገበያ ትስስር ለመፍጠር ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝ የጠቆሙት ዳይሬክተሩ እስከ ጥር 30 ቀን 2012 ዓ.ም  ባለው ጊዜ ከ122 ሺህ 780 ኩንታል በላይ የታጠበና ቅሽር የቡና ምርት ለማዕከላዊ ገበያ መቅረቡን ገልጸዋል። በዞኑ የጎደር ወረዳ የካቦ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት አርሶ አደር ገራፊ አውለው በሰጡት አስተያየት በምርት ዘመኑ የቡና ማሳቸው የተሻለ ምርት ይዞ የነበረ ቢሆንም በጉልበት ሰራተኛ እጦትና ወቅቱን ባልጠበቅ ዝናብ ለብልሽት መዳረጉን ተናግረዋል። በተለይም በኩታ ገጠም ሸካ ዞን ተፈጥሮ በነበረው የጸጥታ ችግር ምክንያት የጉልበት ሰራተኛ እጥረት ማጋጠሙንና ወቅቱን ካልጠበቀ ዝናብ  ጋር ተዳምሮ ምርቱ ሳይሰበሰብ በማሳ ላይ መቅረቱን ገልጸዋል። በምርት ዘመኑ ከጉልበት ሰራተኛ እጥረትና ወቅቱን ካልጠበቀ ዝናብ ችግር በተጨማሪ የኬሻ አቅርቦት ችግርም እንደነበረ የገለጹት ደግሞ በዚሁ ወረዳ የጨሚ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት አርሶ አደር አብዱ ሁሴን ናቸው። በአካባቢው በነበረው የቡና ኬሻ እጥረት ምክንያት በቡና ምርት አያያዝና ጥራት ላይ ችግር መፍጠሩንም ገልጸዋል። እንደ አርሶ አደሮቹ ገለፃ በጠቀሷቸው ችግሮች ምክንያት በምርት ዘመኑ የቡና ምርት በብዛትም ሆነ በጥራት ካለፈው ዓመት ቀንሷል ። በዞኑ በቀዳሚው ዓመት ከ386 ሺህ ኩንታል በላይ የቡና ምርት ተገኝቶ እንደነበር ከክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ቢሮ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም