የብሔራዊ በጎ ፈቃድ አገልግሎት ማብሰሪያ ፕሮግራም ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በተገኙበት እየተካሄደ ነው

130
አዲስ አበባ የካቲት 15/212  የብሔራዊ በጎ ፈቃድ ማብሰሪያ መርሃ ግብር ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በተገኙበት በአፍሪካ ሕብረት እየተካሄደ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ፣ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን የሰው ሀብት፣ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ኮሚሽነር ሳራ ምቢ ኢኖው አንያንግ፣ የክልል ርዕሳነ መስተዳድሮችና ሚኒስትሮች በተገኙበት ፕሮግራሙ በይፋ ተበስሯል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት፤ መርሃ ግብሩ አገራዊ አንድነት፣ ማህበረሰባዊ ትስስር ማሻሻልና አገራዊ ሰላም ለማምጣት ሚናው ከፍተኛ ነው። ወጣቶቹ በቆይታቸው የህይወት ተሞክሮ የሚያገኙበትና የአገራቸውን አካባቢ የሚያውቁበት ነው ሲሉም ተናግረዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወጣቶች የሚሰሩት ስራ መቼ እና የት እንደሚከፈል የማይታወቅ ኢንቨስትመንት መሆኑን አመልክተዋል። ''የበጎ ፈቃድ ስራው ለወጣቶች አንድ ቀን የሚታጨድ ፍሬ ነው'' ብለዋል። ራስን ከመንከባከብ ይልቅ ለሌሎች ዕውቀትንና ሀብትን ማካፈል ራሳቸውን ሰውተው አገር እንዳቆዩ ጀግኖች ሁሉ በጎ ስራም ጀግንነት ነው ብለዋል። የሰላም ሚኒስትር ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል በበኩላቸው "ኢትዮጵያ የወጣቶች አገር ናት፤ ይህን እምቅ ሀብት መግራትና ማበልፀግ ያስፈልጋል" ነው ያሉት። በየዘመኑ ወጣቶች ሀገርን ከጠላት በመከላከልና በልዩ ልዩ ማህበራዊ አገለግሎት መሳተፋቸውን አስታውሰው፤ ''ይህ ትውልድ ሀገርን ማገልገልና ኢትዮጵያን ወደ አዲስ ምዕራፍ ማሻገር ይጠበቅበታል'' ብለዋል። ከ10 ሺህ በላይ የዩኒቨርሲቲና የቴክኒክ ኮሎጅ ምሩቃን፣ ስራ ፈላጊ ወጣቶች የሚሳተፉበት የበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ፤ የአንድ ዓመት ከሁለት ወራት ቆይታ ይኖረዋል። በመጀመሪያዎቹ  ሁለት ወራት ለወጣቶቹ የልቦና ውቅር፣ አካላዊና ምግባራዊ ስልጠና የሚሰጥ መሆኑ ተጠቁሟል። በፕሮግራሙ የተለያዩ የበጎ ፈቃድ ስራዎችን በመስራት የታወቁ ግለሰቦች ወጣቶችን አገር ወዳድ በመሆን ለሰላም፣ ለደግነት፣ ለፍቅርና ለአብሮነት እሴቶች እንዲቆሙ መክረዋል። ወጣቶቹ የተሻለ አበርክቶ እንዲያደርጉ የስብዕናና የክህሎት ስልጠና እንደሚሰጣቸውም  ወይዘሮ ሙፈሪያት አረጋግጠዋል። የበጎ ፈቃድ አገልግሎት አምባሳደሮቹ  በጠቅላይ ሚኒስትሩ ዕዉቅና ተበርክቶላቸዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም