ብልጽግና ፓርቲን በመደገፍ የድርሻቸውን እንደሚወጡ የምዕራብ ጉጂ ዞን ነዋሪዎች ገለጹ

61
ነገሌ የካቲት 15/2012 (ኢዜአ) የህግ የበላይነትን ተከብሮ ዘላቂ ሰላም እንዲመጣ ብልጽግና ፓርቲን በመደገፍ የድርሻቸውን እንደሚወጡ የምዕራብ ጉጂ ዞን ነዋሪዎች ገለጹ፡፡ ነዋሪዎቹ በጠቅላይ ሚኒስተር ዶክተር አብይ አህመድና በፓርቲያቸው ብልፅግና የተጀመሩ የሰላም አማራጮችን በመደገፍ ትናንት በቡሌ ሆራ ከተማ የድጋፍ ሰልፍ አካሔደዋል፡፡ በድጋፍ ሰልፉ ላይ የተካፈሉት የከተማው ነዋሪ ወይዘሮ ገነት ለማ በሰጡት አስተያየት ለዘላቂ ሰላም አለመግባባቶችን በውይይትና በድርድር መፍታት ይገባል ብለዋል፡፡ የፈለጉትን ማግኘት የሚቻለው ሀገር ሰላም ሲሆን ነው ያሉት ወይዘሮዋ ፤ በጥላቻ ንግግር ለውጡን ለማደናቀፍ የሚንቀሳቀሱ ወገኖችም ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ መክረዋል፡፡ ባለፉት ሁለት አመታት ያለገደብ በሚዲያ የታየውን የመጻፍና የመናገር ነጻነት ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ የመጣ እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡ ሀገራዊ ለውጡ እንዳይደናቀፍ በጥላቻ ንግግር የተጠመዱ ወገኖችን መክሮ በመመለስ የድርሻዬን እወጣለሁ ብለዋል፡፡ ሌላው የድጋፍ ሰልፉ ተካፋይ አቶ በሽር ባሳየ በበኩላቸው ብሄር ብሄረሰቦች ለዘመናት የገነቡት አብሮነት በጥላቻ ንግግር እንዳይፈርስ ስለ ሰላም አስፈላጊነት ለወጣቱ እያስተማርን ነው ብለዋል፡፡ ለውጡ ያመጣው ነጻነት ተጠቅመው በዘርና በሀይማኖት እየከፋፈሉ የጥላቻ ንግግር የሚያስተላልፉ ሚዲያዎች ህዝብና ሀገርን እያሰቡ እንዲሰሩ ጠይቀዋል፡፡ አስተያየት ሰጪዎቹ አገራችንን ወደ ላቀ ሰላምና እድገት እንድትሸጋገር የብልፅግና ፓርቲንና ጠቅላይ ሚኒስትራችንን በመደገፍ የበኩላችንን ድጋፍ ለማበርከት ዝግጁ ነን ብለዋል ። በድጋፍ ሰልፉ ላይ የተገኙት የምእራብ ጉጂ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አበራ ቡኖ ባሰሙት ንግግር መንግስት በህግ ማእቀፍ የጥላቻ ንግግርን ለማስቀረት እየሰራ ነው ብለዋል፡፡ የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት ህዝብን ከህዝብ በማጋጨት ሀገራዊ ለውጡን ለማደናቀፍ የሚሰሩ አካላት መኖራቸውን መንግስት ሙሉ መረጃ እንዳለው  ገልጸዋል፡፡ የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት ያልተገደበ ነጻነት ቢሰጥም ህዝብና ሀገር የሚጎዳ ተግባር ሲፈጸም መንግስት እጁን አጣጥፎ እንደማይቀመጥ አብራርተዋል፡፡ ከተቋቋመ አጭር ጊዜ ቢሆንም ብልጽግና ፓርቲ ድንቁርናና ኋላቀርነትን በማስቀረት በሰላምና በልማት የሀገራችንን ከፍታ ለማረጋገጥ እየሰራ ነው  ብለዋል፡፡ የህግ የበላይነት እንዲከበርና ዘላቂ ሰላም እንዲመጣ በምእራብ ጉጂ ዞን ህዝብ ለተጀመረው ድጋፍና ትብብር ምስጋና አቅርበዋል፡፡ በሰላማዊ ሰልፉ ከ10 ሺህ በላይ ህዝብ ተሳትፎበታል ።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም