በቡራዩ በተከሰተው ጥቃት የተጠረጠሩ 17 ሰዎች ቁጥጥር ስር መዋላቸውን ፖሊስ አስታወቀ

65
አዲስ አበባ፤ የካቲት 14/2012 ( ኢዜአ) ትናንት በቡራዩ በተከሰተው ጥቃት የተጠረጠሩ 17 ሰዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ፡፡ ኮሚሽኑ ትናንት በቡራዩ በተከሰተውና ለከተማው የአስተዳደርና የጸጥታ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ኮማንደር ሰለሞን ታደሰ ግድያና ለሌሎች ሶስት ሰዎች መቁሰል ምክንያት ጋር በተያያዘ ከማህበረሰቡ ጋር በመሆን ከትናንት እስከ ዛሬ ከሰዓት በተደረገ ፍተሻ ወንጀሉን በማስተባበር፣ የጥቃት ተልዕኮ ወስደው ጥቃቱን የፈጸሙና ጥቃቱ እንዲደርስ በማመቻቸት የተጠረጠሩ 17 ግለሰቦችን በቁጥጥር ስር ማዋሉን አስታውቋል፡፡ በቡራዩ ከተማ አስተዳደር በ4 ሰዎች ላይ ጥቃት የፈጸመው በኦነግ ሸኔ የሚመራው፣ የነፃነት ሰራዊትና አባ ቶርቤ በማለት ራሱን የሚጠራውና በተለያዩ አከባቢዎች ጥቃት የመፈጸም ተልዕኮ ወስዶ እየተንቀሳቀሰ ያለው ቡድን መሆኑን ኮሚሽኑ ማወጣው መግለጫ ገልጿል፡፡ ከኦሮሚያ ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ያገኘነው መረጃ እንደሚያሳየው በዚህ የወንጀል ድርጊት የተጠረጠሩ ግለሰቦችን አድኖ ለሕግ ለማቅረብ  ህብረተሰቡ ላደረገው ተሳትፎ የኦሮሚያ ፖሊስ ምስጋና አቅርቧል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም