ቋሚ ኮሚቴው በአሶሳ ከተማ የተባባሰው ህገ-ወጥ የመሬት ወረራ በአስቸኳይ እንዲያስቆም አሳሰበ

96
አሶሳ ፣ የካቲት 14 / 2012 (ኢዜአ) የአሶሳ ከተማ አስተዳደር በአካባቢው እየተባባሰ የመጣው ህገ-ወጥ የመሬት ወረራ በአስቸኳይ እንዲያስቆም በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክር ቤት የግብርናና አካባቢ ጥበቃ እና ተፈጥሮ ሃብት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አሳሰበ፡፡ ቋሚ ኮሚቴው  አስተዳደሩ የህብረተቡን ማህበራዊና ሌሎች ጥያቄችን ለመመለስ ያከናወናቸው ተግባራትን ገምግሟል፡፡ በተለይም በከተማው የሚፈጸመው ህገ-ወጥ የመሬት ወረራ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ አሳሳቢ ሁኔታ ላይ መድረሱን አመልክተዋል፡፡ የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ አላዬ ስለሺ እንዳሉት በከተማው ዋና ዋና መንገዶች የሚገኙ እግረኛ መንገዶች በግሰቦች እየታጠሩ ይወሰዳሉ። አስተዳደሩ ህገ-ወጥ መሆኑን እያወቀ የግንባታ ፈቃድ እንደሚሰጥ በግምገማ መመልከታቸው ተናግረዋል፡፡ መሬት በማስተላላፍ ሂደት ቅንጅታዊ አሰራር አለመኖሩን የገለጹት ሰብሰቢው አንድ መሃንዲስ ለአንድ ግለሰብ ቦታ ለመምራት ከወጣ በኋላ ለሌሎች ሶስት ሰዎች ተጨማሪ ቦታዎችን በህገ-ወጥ መንገድ አስተላልፎ መገኘቱን ቁመዋል፡፡ በተለይም ከከተማው አቅራቢያ በ2000 ዓ.ም."ኢንዚ ሚሊኒዬም ፓርክ" ተከልሎ በደን ከተሸፈነው ስፍራው አብዛኞው በህገ-ወጥ ግለሰቦች ተወርሮ መወሰዱን አመልክተዋል፡፡ "በህ-ገወጥ መሬት ወረራው የርዕሰ መስተዳድር ጽህፈት ቤት ሠራተኞችና ጸጥታ አስከባሪ አካላትን ጨምሮ አብዛኞቹ ከቀጠና እስከ ክልል የሚገኙ ከፍተኛ አመራሮች ተሳትፈውበታል "ብለዋል፡፡ በከተማው ለግለሰቦች በመሰረተ ልማት የተሟላ ቦታ ሲሰጣቸው የመንግስት ተቋማት ግን በማይመች ቦታ ይዞታ እንደሚዘጋጅላቸው አቶ አላዬ ተናግረዋል፡፡ ጉዳዩ  የከፋ የመልካም አስተዳዳር ችግር ሳያስከትል በአስቸኳይ እንዲስተካከል ሰብሳቢው አሳስበዋል፡፡ የክልሉ ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ መንግስቱ ታከለ የመሬት ወረራው ከመነሻው ጀምሮ አለመገታቱ እንዳባባሰው ጠቅሰው "ችግሩን ለማስወገድ የማያዳግም እርምጃ ይሠራል"ብለዋል፡፡ የአሶሳ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ኡመር አህመድ በበኩላቸው "የህገ-ወጥ መሬት ወረራው መባባስ ምክንያት በአስተዳደሩ የታችኛው መዋቅር ያለው ብልሹ አሰራር ነው" ሲሉ ገልጸዋል፡፡ በአስተዳደሩ በቀጠና አመራር ኃላፊነት ከተነሱ በኋላ ሲሰሩባቸው የነበሩ ማህተሞችን በድብቅ በመውሰድ ሃሰተኛ ሰነዶችን በማዘጋጀት ጭምር እየተሳተፉ የሚገኙትን ጠቅሰዋል፡፡ ችግሩን ለማቆም በክልል በየደረጃው የሚገኙ አካላትንያሳተፈ ኮሚቴ መዋቀሩን አመልክተው የተያዙ  ግልሰቦች እንዳሉም ጠቁመዋል፡፡ በህገ-ወጥ የመሬት ወረራው የተሳተፉ አንዳንድ ከፍተኛ አመራሮች ግን በዛቻ እና ማስፈራሪያ  ስራውን ለማደናቀፍ እየጣሩ መሆኑን  አቶ ኡመር አመልክተዋል፡፡ ከንቲባው የክልሉ መንግስት፣ የስነ-ምግባርና ጸረ-ሙስና ኮሚሽን እና ጠቅላይ አቃቢ ህግን እገዛ ጠይቀዋል፡፡ የአስተዳደሩ አመራሮች ህገ-ወጥ የመሬት ወረራውን ለመገምገም የመጡ የቋሚ ኮሚቴ አባላትን ለወራት በማጉላላት ስራውን እንዲስተጓጎ  ማድረጋቸውን የገለጹት ደግሞ የክልሉ ምክር ቤት ዋና አፈ-ጉባኤ አቶ ሐብታሙ ታዬ ናቸው። የመሬት ወረራውን መባባስ ጉዳይ ከተማ አስተዳደሩ ብቻ ሳይሆን የክልሉ መንግስት እና ሌሎችም ባለድርሻዎች በመቀናጀት በጥናት የተደገፈ ማስተካከያ ማድረግ እንዳለባቸው አስገንዝበዋል፡፡ ሁለት ሺህ 345 ሄክታር የቆዳ ስፋት ያላት አሶሳ ከተማ 100 ሺህ የሚጠጋ ህዝብ እንደሚኖርባት ከአስተዳደሩ የተገኘ መረጃ ያመለክታል፡፡    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም