"መደመር መነሻችን ብልፅግና መድረሻችን" በሚል መሪ ሀሳብ የተዘጋጀ የስፖርት ውድድር ተካሄደ

62
ዲላ፣ የካቲት14/2012 (ኢዜዘ) "መደመር መነሻችን ብልፅግና መድረሻችን" በሚል መሪ ሀሳብ በደቡብ ክልል ጌዴኦ ዞን የተዘጋጀ የስፖርት ውድድርና የተተከሉ ችግኞች እንክብካቤ ተካሂደ። ከስፖርቱ የዞን አመራሮችና የከተማ አስተዳደር የስራ ኃላፊዎች መካከል የእግር ኳስ ውድድር ይገኝበታል። የጌዴኦ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ገዙ አሰፋ በዚህው ወቅት እንዳሉት መረሃ ግብሩ እንደ ሃገር የተጀመረው የብልጽግናና የአንድነት ጉዞ ማሳያ ይሆን ዘንድ የተዘጋጀ  ነው። "ሃገራችን አሁን የጀመረችውን የብለፅግና ጉዞ አጠናክሮ ለማስቀጠል የሕዝቡን አንድነትና መተባበር ይጠይቃል" ብለዋል። የእግር ኳስ ጨዋታና ህዝቡን ያሳተፈ የተተከሉ ችግኞች እንክብካቤ መካሄዱ አመራሩም ሆነ ህዝቡ የለውጥ ጉዞን በመደገፍ የራሱን አሻራ እንዲያስቀምጥ መነሳሳትን ለመፍጠር መሆኑን ተናግረዋል። የህዝቡን እርስ በእርስ መተሳሰብን አጠናክሮ ለመጓዝ ስፖርት ዋነኛ መሳሪያ በመሆኑ በዞንና በከተማ አመራሮች መካከል ይህ ውድድር መዘጋጀቱን የሚገልጹት ደግሞ የዲላ ከተማ የብልፅግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ዳንኤል ታደሰ ናቸው። ውድድሩ የሕዝቦችን የላቀ አብሮነት በማረጋገጥ ለብልፅግና ደጋፊዎችና መላው ህብረተሰብ መልዕክት ለማስተላለፍ፣ ከአመራሩ የዳበረ የአካልና የአዕምሮ ብቃት እንዲኖረው የሚረዳ መሆኑንም አመልክተዋል። የዲላ ከተማ ነዋሪ  አቶ ተካልኝ ታደለ በሰጡት አስተያየት  የተተከሉ ችግኞች እንክብካቤና ስፖርቱ ላይ መሳተፋቸውን ተናግረዋል። የብልጽግና ጉዞ የህዝቦችን አንድነትና ተጋግዞ ማደግ  መርህ  አድርጐ እየተቀሳቀሰ በመሆኑ እሳቸውም ለዚህ ስኬት የድርሻቸውን እንደሚወጡ ገልጸዋል። አዝናኝና ብዛት ያለው ተመልካች  የነበረው የጌዴኦ ዞን አመራሮችና የዲላ ከተማ የስራ ኃላፊዎች መካከል የተደረገው የእግር ኳስ ጨዋታ በዞኑ አመራሮች አንድ ለባዶ አሸናፊነት ተጠናቋል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም