ብሔራዊ አልኮል፣ አረቄ ፋብሪካና ፌዴራል ማረሚያ ቤቶች ተጋጣሚዎቻቸውን አሸነፉ

64
አዲስ አበባ፣ የካቲት 14/2012 (ኢዜአ) በሐበሻ ሲሚንቶ የሴቶች ቮሊቦል ፕሪሚየር ሊግ ሁለተኛ ሣምንት ጨዋታዎች ብሔራዊ አልኮል፣ አረቄ ፋብሪካና ፌዴራል ማረሚያ ቤቶች ተጋጣሚዎቻቸውን አሸነፉ። የሊጉ መርሀ ግብሮች ዛሬ በአዲስ አበባ ትንሿ ሁለገብ ስታዲየም ተካሂደዋል። በመጀመሪያው ጨዋታ ብሔራዊ አልኮልና አረቄ ፋብሪካ የሊጉን አዲስ ተሳታፊ ወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲን በሦስት የጨዋታ ክፍለ ጊዜ 3 ለ 0 አሸንፏል። የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ የአንድ ቡድን የበላይነት የታየበትና ተመጣጣኝ ፉክክር ያልነበረበት ነው። ውጤቱን ተከትሎ ብሔራዊ አልኮልና አረቄ ፋብሪካ በሊጉ ሁለተኛ ድሉን ሲያስመዘግብ ወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ በፕሪሚየር ሊጉ የመጀመሪያ ሽንፈቱን አስተናግዷል። በሌላ የሊጉ መርሀ ግብር ፌዴራል ማረሚያ ቤቶች ጌታዘሩ ስፖርት ክለብን በአራት የጨዋታ ክፍለ ጊዜ 3 ለ 1 በሆነ ውጤት ማሸነፍ ችሏል። የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ አንጻራዊ በሆነ መልኩ ጥሩ የሚባል ፉክክር የታየበት ሲሆን የተመልካቹን ትኩረት የሳበ ነበር ማለት ይቻላል። ውጤቱን ተከትሎ ፌዴራል ማረሚያ ቤቶች በሊጉ የመጀመሪያ ድሉን ሲያስመዘግብ፤ ጌታዘሩ ስፖርት ክለብ ሁለተኛ ሽንፈቱን አስተናግዷል። የሐበሻ ሲሚንቶ ቮሊቦል ፕሪሚየር ሊግ ቀጣይ መርሀ ግብር ከሁለት ሣምንት በኋላ እንደሚካሄድ ታውቋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም