የእናቶችና የጨቅላ ህፃናትን ሞት ለመቀነስ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ተጠየቀ

48

አዲስ አበባ፣የካቲት14/2012 (ኢዜአ) የእናቶችና የጨቅላ ህፃናትን ሞት ለመቀነስ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች የድርሻቸውን እንዲወጡ ተጠየቀ። በየዓመቱ ከጥር 1 ቀን ጀምሮ ለአንድ ወር የሚከበረው የጤናማ እናትነት ወር ዘመቻ በዓለም ለ33ኛ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ14ኛ ጊዜ "እናት የቤተሰብና የአገር ምሰሶ ናት" በሚል መሪ ሃሳብ ተከብሯል።

የጤና ሚኒስቴር ጤናማ እናትነትና የጨቅላ ህፃናትን ሞት መቀነስ በሚሉት ሃሳቦች ላይ ለመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች የአንድ ቀን የግንዛቤ ማስጨበጫ መርሃ ግብር አዘጋጅቷል።

በሚኒስቴሩ የእናቶችና ህጻናት ዳይሬክተር ዶክተር መሰረት ዘለለ እንደገለጹት በአገሪቷ 50 በመቶ የሚሆኑት ነፍሰ ጡር እናቶች የሚወልዱት በጤና ተቋማት ነው።

ቀሪዎቹ 50 በመቶ እናቶች በቤት ውስጥ ያለጤና ባለሙያ እገዛ እየወለዱ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

ይህም እናቶችና ጨቅላ ህፃናትን ለከፍተኛ ችግርና ለሞት አደጋ እየዳረገ መሆኑን ነው የገለጹት።

ዶክተር መሰረት እንዳሉት ሚኒስቴሩ የእናቶችና ጨቅላ ህፃናትን ሞት ለመቀነስ የጤና ተቋማትን ከማስፋፋት በተጨማሪ የጤና ባለሙያዎችን በብዛት በማሰልጠን ላይ ይገኛል። ለወሊድ አገልግሎት የሚሆኑ ግብዓቶችና አምቡላንሶችን ለጤና ተቋማት እያሟላ መሆኑንም ነው ያስረዱት።

ሚኒስቴሩ የእናቶችና ጨቅላ ህፃናትን ሞት ለመቀነስ ለሚያከናውናቸው ተግባራት የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ሙያዊ ድጋፍ እንዲያደርጉም ጠይቋል።

የእናቶችና ጨቅላ ህፃናትን ጤና የተመለከቱ ተከታታይ ዘገባዎችና ፕሮግራሞችን በመስራት የኅብረተሰቡን ግንዛቤ ማሳደግ እንደሚጠበቅባቸውም አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም