የባህርዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም ካፍ ያስቀመጠውን መስፈርት ማሟላቱ ተገለፀ

79
ባህር ዳር ኢዜአ 13/06/2012 የባህርዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም ካፍ የጠየቀውን መሰረተ ልማት ቀድሞ ማሟላት መቻሉን የአማራ ክልል ስፖርት ኮሚሽን አስታወቀ። የአፍሪካ እግር ኳስ ፌደሬሽንካፍ/ ገምጋሚ ቡድን በመጭው ሚያዚያ ወር መጀመሪያ የስታዲየሙን መሰረተ ልማት በመጎብኘት የመጨረሻ ውሳኔ ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል። በኮሚሽኑ የስፖርት ፋሲሊቲ ዳይሬክተር አቶ ባንተአምላክ ሙላት ለኢዜአ እንደገለጹት ስታድዮሙ እስከ አሁን ድረስ ከ580 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ተደርጎበታል። በካፍ ገምጋሚ ቡድን እንዲሟሉ የተጠየቁት የተጫዋቾች፣ አሰልጣኞች፣ ዳኞችና ኮሚሽነሮች የመልበሻ ክፍሎች ፣ የኮንፈረንስ አዳራሽ ፣ የጋዜጠኞች መከታተያና ሌሎች መሰረተ ልማቶች እንዲሟሉለት ተደርጓል። የተጫዋቾች ህክምናና ምርመራ የሚያካሔዱበት ክፍሎች፣ሁለት የመለማመጃ ሜዳዎች፣ የተጫዋቾች ልብስ መቀየሪያና ሌሎች ክፍሎች ደረጃቸውን በጠበቀ መልኩ ማሟላት ተችሏል። የፖሊስ ባለሙያም ሆነ አመራር ጨዋታዎችን የሚቆጣጠሩበት አመቺ ክፍል ከመዘጋጀቱም በላይ 26 የደህንነት ከሜራዎች መገጠማቸውን ተናግረዋል። አደጋ ቢከሰት በድምጽና በመብራት ጥሪ የሚያሰሙና ምልክት የሚያሳዩ የአደጋ መከላከያ መሳሪያዎች ከመገጠማቻው ባሻገር የተከሰተውን የእሳት አደጋ ሊያጠፋ የሚችል የውሃ ማከማቻ ታንከር መገንባቱን አስታውቀዋል። በአሁኑ ወቅትም በስታዲየሙ በሚካሄዱ የእግር ኳስ ጨዋታዎች መብዛት የተነሳ የተጎዳውን የሜዳ ሳር የማስተካከል ስራ እየተሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል። ይሁን እንጂ ቡድኑ አስተያየት ከሰጠባቸው ውስጥ በማታ ጨዋታ ለማካሄድ የሚያስችል የመብራት ባውዛ ገጠማው ከጊዜ፣ ከወጭና አስገዳጅም ካለመሆኑ ጋር ተያይዞ አለመሰራቱን ተናግረዋል። ይህም ከ60 ሚሊየን ብር በላይ ወጭ ከመጠየቁም ባለፈ የስታዲየሙ ጣራ ሳይገጠም የሚተከለው ባውዛ በኋላ የሚፈርስ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ኪሳራ የሚያስከትል በመሆኑ መታለፉን አመልክተዋል። የተገነባውን የፍሳሽ መጠራቀሚያሴፍቲ ታንከር/ ውሃ በማያሰርግ ኬሚካል ማልበስ በመቻሉ በስታዲየሙ ውስጥ የሚገኙ 360 መጸዳጃ ቤቶችን በቅርቡ ለተመልካቹ ክፍት ይደረጋሉ ተብሏል። የስታዲየሙን ወንበር ለመግጠም የሚያስችል ገንዘብ መገኘቱን የገለፁት ዳይሬክተሩ በመጀመሪያ የጣራ ስራውን ማከናወን ተመራጭ በመሆኑ ሊዘገይ መቻሉን ገልፀዋል። በመሆኑም የካፍ ጋምጋሚ ቡድን ቀደም ሲል እንዲሟሉ በሚል የሰጣቸውን አስተያየቶች  መሰረት በማድረግ ማሟላት መቻሉን ጠቅሰው በመጪው ሚያዚያ ወር በስታድየሙ በመገኘት የመጨረሻ ውሳኔ ይሰጣልም ተብሎ እንደሚጠበቅ አብራርተዋል። የጣራ ስራውን ለማከናወን 600 ሚሊየን ብር የሚያስፈልግ ሲሆን በክልሉ መንግስትና በህዝቡ ያለውን በጎ ፈቃድ በመጠቀም በቀጣይ ይሰራል ብለዋል ።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም