የኢትዮ ኤርትራ የሰላም ድርድር በህዝብ ለህዝብ ውይይት ሊታገዝ ይገባዋል- ኤርትራውያን ስደተኞች

72
ሽሬ እንዳስላሴ ሰኔ 20/2010 የአትዮ - ኤርትራ የሰላም ውይይት ከመንግስታት ባለፈ በሁለቱም ህዝቦች የፊት ለፊት ህዝባዊ መድረኮች ሊታገዝ እንደሚገባው በኢትዮጵያ የሚገኙ ኤርትራውያን ስደተኞች ጠየቁ፡፡ ስደተኞቹ ለኢዜአ እንደገለጹት ለሁለቱ ህዝቦች መለያየት ምክንያት የሆነው የድንበር ግጭት ጉዳይ እልባት እንዲያገኝ በሁለቱ አገራት መንግስታት በኩል የተጀመረው ውይይት የደስታ ስሜት አጭሮባቸዋል። በሁለቱም አገሮች መካከል ላለፉት 20 ዓመታት የቆየው አለመግባባትና ቅራኔ በመልካም ግንኙነት እንዲቀየር ከፍትኛ ፍላጎት እንዳለቸውም ኤርትራውያኑ ተናግረዋል፡፡ በትግራይ ሰሜን ምዕእራብ ዞን ከሚገኙ ኤርትራውያን ስደተኞች መካከል ወጣት ቶፊቅ ኑርሁሴን እንዳለው በአገሮቹ መካከል ዘላቂ ሰላም እንዲመጣ መንግስታቱ እያደረጉት ካለው ግንኙነት በተጨማሪ በሁለቱም ህዝቦች መካከል ውይይት ሊካሄድ ይገባል። ውይይቱ ዘላቂ ሰላም ከማምጣቱ ባለፈ አገራቸውን ጥለው ስደት ላይ የሚገኙ ኤርትራውያንን ተጠቃሚ ስለሚያደርግ በሁለቱ መንግስታት በኩል ትኩረት እንዲሰጠው ጠይቋል። በሁለቱ ሀጋራት የነበረውን ችግር በዘላቂነት የመፍታቱ ጉዳይ በድንበር አካባቢ ያሉ ህዝቦች የተረጋጋ ሕይወት እንዲመሩ ያስችላልም ብሏል ወጣት ቶፊቅ፡፡ በኢትዮ ኤርትራ መካከል የሰላም ውይይት መጀመሩ ለሁለቱም ሀገራት ተጠቃሚ እንደሚያደርግ የገለጹት ደግሞ አቶ ፍስሀ ዓንደማሪያም የተባሉ ኤርትራዊ ስደተኛ ናቸው፡፡ በድንበር ላይ የነበረውን አለመግባባት ለመፍታት የተጀመረውን እንቅስቃሴ አድንቀው “የሁለቱ አገራት መንግስታት እያደረጉት ባለው ጥረት ላይ ህዝቦች ቢታከሉበት ቅድሚያ በስደት ላይ የምንገኝ ኤርትራውያን ተጠቃሚ ነን” ብለዋል፡፡ ወጣት አስመረት ፍስሃፅዮንም “በሁለቱ ወንድማማች ህዝቦች መካከል ውይይትና መቀራረብ እንዲኖር ማድረግ የነበረውን ቅራኔ ዘላቂ በሆነ መንገድ ለመፍታት ያስችላል”፡፡ በትግራይ ሰሜናዊ ምዕራብ ዞን በሚገኙ አራት መጠለያ ጣቢያዎች ከ180 ሺህ በላይ ኤርትራውያን ስድተኞች ተጠልለው እንደሚገኙ ከዞኑ የስደተኞችና ከስድት ተመላኞች ጉዳይ አስተዳደር ፅህፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም