ቅርንጫፎቹ በበጀት ዓመቱ ከ3 ቢሊዮን 300 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ሰበሰቡ

55
መቀሌ፣ የካቲት 14/2012(ኢዜአ) በገቢዎች ሚኒስቴርና ጉምሩክ ኮሚሽን የመቀሌ ቅርንጫፎች በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያዎቹ ስድስት ወራት ከ3 ቢሊዮን 300 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ በመሰብሰብ ከእቅድ በላይ አከናወኑ። በገቢዎች ሚኒስቴር የመቀሌ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ስራ አስኪያጅ አቶ ተክላይ አብርሃ ለኢዜአ እንደገለጹት በግማሽ የበጀት ዓመቱ  አንድ ቢሊዮን 500 ሚሊዮን ብር ተሰብስቧል። ይህም ከእቅዱ  በ200 ሚሊዮን ብር ብልጫ አለው። የተሰበሰበው ገቢ ቀጥታ ካልሆነ ግብር ፣ ከተጨማሪና ከአገልግሎት  እሴት ታክስ  የተገኘ መሆኑን አመልክተዋል። ገቢው ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸርም በ24 በመቶ ብልጫ እንዳለውም ጠቁመዋል። ለገቢው መጨመር የግብር ከፋይ ነጋዴዎች በታክስ ያለው ግንዛቤ እየጨመረ በመምጣቱ እንዲሁም  በወቅቱ ለሚከፍሉ ነጋዴዎች ደግሞ የማበረታቻ የእውቅና ሽልማት መሰጠቱ ለገቢ መጨመር አስተዋጽኦ ማድረጉን ጠቅሰዋል። ጥሩ ስነ ምግባርና የተሻለ አፈፃፀም ያላቸው የቅርንጫፉ ጽህፈት ቤቱ ሰራተኛች እውቅ በመሰጠቱ የስራ ተነሳሽነታቸው እንዲጨምር አድርጓል። ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቱ በግብር ስርዓቱ ህግ የማስከበር ስራ መከናወኑ፣ ደንበኞች የሚያነሷቸው ቅሬታዎች በወቅቱና በአግባቡ መፍታትም የተሻለ አፈፃፀም ለማሳየት ማገዙንም አቶ ተክላይ አስረድተዋል። በፌዴራል ጉምሩክ  ኮሚሽን የመቀሌ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ከአንድ ቢሊዮን 800 ሚሊዮን ብር በላይ ከቀረጥና ሌሎች አገልግሎቶች ገቢ መሳብሰቡን ገልጸዋል። የቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቱ ምክትል ስራአስኪያጅ አቶ በሪሁ ተስፋይ እንዳሉት ገቢው ከእቅዱ በ600 ሚሊዮን ብር ብልጫ ያለው ነው። ኮሚሽኑ ገቢው ያገኘው ወደ አገር ውስጥ ከሚገቡ የግንባታ፣ ከምግብና ምግብ ነክ ከሆኑ እቃዎች እንደሆነ አመልክተዋል። የንግዱ ማህበረሰብ ግንዛቤ እያደገ በመምጣቱንና አካባቢው የተረጋጋ መሆኑን ተከትሎ የኢንቨስትመንት ፍሰቱ በመጨመሩ ለገቢው ማደግ አስተዋጽኦ አድርጓል። በኮንትሮባንድ የሚገቡ እቃዎችም ከክልሉ የጸጥታ ኃይል ጋር ቁጥጥሩ በመጠናከሩ ለክንውኑ መጨመር ሌላው ምክንያት እንደሆ ተጠቅሷል። ለፌደራል ገቢዎች ዓመታዊ ግብር ከሚከፍሉ መካከል ቢን መስከረም ሆስፒታል ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ስራ አስኪያጅ ወይዘሮ አልማዝ  መስፍን በሰጡት አስተያየት ለሚሰጧቸው አገልግሎቶች ከደረሰኝ ውጭ እንደማይፈጽሙ ተናግረዋል። ሆስፒታሉ የግብር አከፋፈል ህግ በማክበርና ግልፅ አሰራር በመከተል ለፌዴራል መንግስት ግብር እንደሚከፍል ገልጸዋል። ባለፈው ዓመት ከ 1ሚሊዮን ብር በላይ ግብር በወቅቱ በመክፈል ምስጉን ተቋም ተብሎ የእውቅና የምስክር ወረቀት እንደተሰጣቸውም ጠቅሰዋል። ከሆስፒታሉ ባለቤቶች የትርፍ ክፍፍል ላይም ለፌደራል ገቢዎች 283ሺህ ብር መከፈሉንም ስራአስኪያጇ አመልክተዋል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም