የጥፋት ሃይሎችን ሴራ በማክሸፍ ሰላምና መረጋጋትን ለመፍጠር እንደሚሰራ ፖሊስ ገለጸ

113

የካቲት 14/2012 (ኢዜአ) የጸጥታው ሃይል የጥፋት ሃይሎችን ሴራ በማክሸፍ የህዝቡን ሰላምና መረጋጋትን ለማረጋገጥ ያለ እረፍት እንደሚሰራ የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን ገለጸ።

በቡራዩ ከተማ አስተዳደርና ጸጥታ ክፍል ሃላፊ እንዲሁም በሌሎች ሰዎች ላይ ጥቃት በማድረስ ህይወት ያጠፉ አካላትን ተከታትሎ እርምጃ እንደሚወስድም አስታውቋል።
 
ኮሚሽኑ ባወጣው መግለጫ የቡራዩ ከተማ የአስተዳደር ጸጥታ ክፍል ሃላፊ አቶ ሰለሞን ታደሰ ትናንት በተፈፀመባቸው ጥቃት ህይወታቸው ማለፉን ገልጿል።
 
በእለቱ በአራት ሰዎች ላይ በተፈጸመ ጥቃት የጸጥታ ክፍል ሃላፊው ህይወት ወዲያውኑ ያለፈ ሲሆን ሌሎች ሶስት ሰዎች ጉዳት ደርሶባቸው በህክምና እየተረዱ እንደሆነም በመግለጫው ተገልጿል።
 
ከጥቃቱ ጋር በተያያዘ ፖሊስ የምርመራ ስራ መጀመሩን ኮሚሽኑ ባወጣው መግለጫ ገልጿል።
 
የህግ የበላይነትን ለማስከበርና ወንጀለኞችን አድኖ በመያዝ ለፍርድ ለማቅረብ ቀን ከለሊት እንደሚሰራም አረጋግጧል።
ኮሚሽኑ ህዝቡ ደህንነቱ እንዲረጋገጥ ከመንግስት አካላት ጋር በንቃት አብሮ እንዲሰራ ጥሪ አቅርቧል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም