የአፍሪካ የጤና ሚኒስትሮች በኮሮና ቫይረስ ዙሪያ አስቸኳይ ስብሰባ ተቀምጠዋል

56
አዲስ አበባ፣ የካቲት14/2012(ኢዜአ) ውይይቱ ስለ ኮቪድ አዳዲስ መረጃዎችን ለመለዋወጥ፣ ወረርሽኙን በአህጉር ደረጃ በቅንጅት ለመከላከልና ምላሽ ለመስጠት የተጠራ አስቸኳይ የአፍሪካ የጤና ሚኒስትሮች ጉባዔ ነው። ሚኒስትሮቹ በወረርሽኙ ዙሪያ የተቀናጀ አህጉራዊ የመከላከልና ለበሽታው ምላሽ የመስጠት ስትራቴጂ ላይ ስምምነት መድረስ የሚያስችል ውይይት ያካሂዳሉ። በተጨማሪም በቻይና ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ ያሉ አፍሪካዊያን ተማሪዎችና ዜጎች ወደ አገራቸው መመለስ በሚችሉበት ሁኔታ ላይም እየመከሩ ነው። ለበሸታው እየተደረጉ ያሉ የመድሃኒት ምርምሮች፣ ክትባቶችና በሽታውን ለመከላከልና ለመቆጣጠር እየተሰሩ ባሉ ስራዎች ላይ የልምድና የመረጃ ልውውጥ እንደሚያደርጉም ይጠበቃል። የዓለም የጤና ድርጅት ኮሮና ተህዋሲ /ኮቪድ-19/ ወረርሽኝን ባለፈው የፈረንጆቹ ጥር ወር 'ዓለም አቀፍ የጤና ጠንቅ' ሲል ማወጁ ይታወሳል። ወረርሽኙ በፍጥነት እየተስፋፋ ቻይናን ጨምሮ 25 አገራትን አጥቅቷል፤ ከአፍሪካ አህጉርም ግብጽ በበሽታው የተጠቃ የመጀመሪያ ሰው በአገሯ ስለመገኘቱ ይፋ ማድረጓ ይታወቃል። በሽታው በአህጉሪቷ እንዳይስፋፋ የተቀናጀ መከላከልና ምላሽ መስጠትን ዓላማ ያደረገው የአፍሪካ ጤና ሚኒስትሮች አስቸኳይ ጉባዔም ይህን ተከትሎ ነው የተጠራው። የዓለም የጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ቴድሮስ አድሀኖም ከጄኔቭ በቪዲዮ ኮንፍረንስ በቀጥታ በመድረኩ እየተሳተፋ ነው። የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፈቂ መሀማት እና የጤና ሚኒስትር ዴኤታዋ ዶክተር ሊያ ታደሰ በጉባዔው ላይ ተገኝተዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም