ብሔራዊ የበጎ ፍቃድ የማኅበረሰብ አገልግሎት መርሃ ግብር እሑድ ይጀመራል - የሠላም ሚኒስቴር

58
አዲስ አበባ (ኢዜአ) የካቲት 13/2012 በኢትዮጵያ አገራቸውን የሚወዱና የአገልጋይነት ስሜት የተላበሱ ወጣቶችን ለማፍራት ያለመ ብሔራዊ የበጎ ፈቃድ የማኅበረሰብ አገልግሎት መርሃ ግብር ሊጀመር ነው። ለአገልግሎቱ አምስት የበጎ ፈቃድ አምባሳደሮች ተመርጠዋል፤ ከመላ አገሪቷ የተውጣጡ ከ116 ሺህ በላይ ወጣቶችም ተመዝግበዋል። የሠላም ሚኒስቴር ከነገ በስትያ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድና ከተለያዩ የአገሪቷ ክፍሎች የሚውጣጡ ከሁለት ሺህ በላይ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች በሚገኙበት በይፋ ስለሚጀመረው መርሃ ግብር ዛሬ መግለጫ ሰጥቷል። የበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ የሚሰጠው መንግስታዊ ካልሆኑ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ጋር በመተባበር እንደሆነም ተገልጿል። በሠላም ሚኒስቴር የተጠሪ ተቋማትና ስትራቴጂክ አጋርነት ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ዳይሬክተር ጄኔራል ወይዘሮ አስማ ረዲ እንዳሉት፤ መርሃ ግብሩ የዜጎችን አብሮ የመኖር እሴት ያዳብራል። ከ116 ሺህ በላይ ወጣቶች መመዝገባቸውን የገለጹት ወይዘሮ አስማ፤ በሚቀጥሉት ሁለት ሳምንታት አስር ሺህ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች በመጀመሪያው ዙር ለሁለት ወራት ይሰለጥናሉ ብለዋል። ወጣቶች የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በመስጠታቸው ከሚያገኙት እርካታ በተጨማሪ በተለያዩ ተቋማት መቀጠር የሚያስችላቸው የስራ ልምድ ይሰጣቸዋል ብለዋል። የበጎ ፈቃድ አገልግሎትን በተቋም ደረጃ በማሳደግ መርሃ ግብሩ ውጤታማና ዘላቂ እንዲሆን ለማድረግ እንደሚሰሩም ገልጸዋል። የበጎ ፈቃድ አምባሳደር ሆነው የተመረጡት ኡስታዝ ያሲን ኑሩ ለስልጠና የተዘጋጁት ሞጁሎች በወጣቶች ስብዕና ግንባታ ላይ የሚያተኩሩ መሆናቸውን ተናግረዋል። በኢትዮጵያ 'ውጤቱን እንጂ የውጤቱን መገኛ መንገድ የመፈለግ ልምድ አናሳ ነው' ከሚባለው አስተሳሰብ መውጣት እንደሚገባም ተገልጿል። በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ ባለመገኘታቸው ስማቸው ያልተጠቀሰን አንድ ግለሰብ ጨምሮ ሲስተር ዘቢደር ዘውዴ፣ ኡስታዝ ያሲን ኑሩ፣ ወይዘሮ ፊልሰን አብዱላሂና ፓስተር ዮናታን አክሊሉ የበጎ ፈቃድ አምባሳደሮች ሆነው ተመርጠዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም