ሀገራዊ የለውጥ እንቅስቃሴን እንደግፋለን... የሀረና ወረዳ ነዋሪዎች

64

ጎባ፤ ኢዜአ የካቲት 13/2012 በባሌ ዞን የሀረና ወረዳ ነዋሪዎች ሀገራዊ የለውጥ እንቅስቃሴ ከዳር እንዲደርስ የሚደግፉ መሆናቸውን ገለጹ። ነዋሪዎቹ ድጋፋቸውን የገለጹት ዛሬ በአንጌቱ ከተማ በመሰባሰብ ባካሄዱት ሰልፍ ነው።

 " በመንደርተኝነት አስተሳሰብ የኦሮሞ ህዝብ ለመከፋፈል የሚጥሩትን እንቃወማለን፣የተጀመሩ ሀገራዊ ለውጦች ከዳር እንዲደርሱ እንደግፋለን፣ ከሀገር አልፎ ምስራቅ አፍሪካን ላስተሳሰረ መሪያችን ድጋፍ እንሰጣለን" የሚሉ መፈክሮች ሰልፈኞቹ አስተጋብተዋል።

ከሰልፈኞቹ መካከል አቶ ኡስማን ገልቹ በሰጠው አስተያየት ባለፉት ሁለት ዓመታት የተመዘገቡ ውጤቶች ሀገሪቱ በእድገትና ዲሞክራሲ ለውጥ ላይ እንዳለች ማሳያ መሆኑን ተናግረዋል።

ከሀገር አልፎ በአፍሪካ ቀንድ ሀገራት መካከል አንድነት እና ወዳጅነት እንዲጠናከር ዶክተር አብይ አህመድ ላበረከቱት አስተዋጽኦ ኢትዮጵያዊያን እውቅናና ድጋፍ ሊሰጡ እንደሚገባም አመልክተዋል።

ሰላም፣ልማትና ዲሞክራሲ ተረጋግጦ ኢትዮጵያ የአፍሪካ ተምሳሌት እንድትሆን ብልፅግናን እንደሚደግፉ የተናገሩት ደግሞ ሌላው ሰልፉ ተሳታፊ አቶ አብዱሰላም ማማ ናቸው፡፡

በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ መሪነት የሀገሪቱን ሁለንተናዊ ችግሮችን ለመፍታት እያደረጉ ያሉትን ጥረት ለመደገፍና እውቅና ለመስጠት የድጋፍ ሰልፍ መውጣታቸውን ተናግረዋል፡፡

አቶ ሀሰን አልይ በበኩላቸው ዶክተር አቢይ አህመድ በአጭር ጊዜ ውስጥ ለሰላም፣ ፍቅርና አንድነት የሰጡት ዋጋና የመጣው ለውጥ ሊደጋፉ ሰልፍ እንደወጡ ገልጸዋል፡፡

"ለህዝቦች ነፃነት፣ ለእውነትና አንድነት የቆመ የኢትዮጵያ መሪ መሆናቸውን በአጭር ጊዜ ውስጥ በተግባር ባከናወኗቸው ሥራዎችና ባመጧቸው ለውጦች አረጋግጠናል" ብለዋል።

የሀረና ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሁሴን መሐመድ የመደመር አስተሳሰብ የኢትዮጵያን ህዝቦች አንድነት ለማዳበር ምቹ ሁኔታ የፈጠረ መሆኑን ለሰልፈኞቹ ተናግረዋል።

በሀገሪቱ የተጀመሩ ለውጦች ከዳር እንዲደርሱ ህብረተሰቡ ድጋፉን ማጠናከር እንዳለበት አሳስበዋል።

“የተጀመሩ ሀገራዊና ክልላዊ ለውጦች ከዳር እንዲደርሱ ሁሉም የዞኑ ነዋሪዎች በአንድነት ሊቆሙ ይገባል” ያሉት ደግሞ የባሌ ዞን አስተዳደር ተወካይ አቶ ገና አሎ ናቸው።

የልማትና መልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ፈጣን ምላሽ ለመስጠትም እንዲቻል ሁሉም ነዋሪዎች ከመንግስት ጎን በመቆም እንዲደግፉ ጠይቋል፡፡

በባሌ ዞን ተመሳሳይ የድጋፍ ሰልፎች ከሀረና በተጨማሪ በሲናና ፣በርበሬና ጋሰራ ወረዳ መካሄዳቸውን ከዞኑ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም