በጋምቤላ ክልል የተቀናጀ የገጠርና ከተማ መሬት አያያዝና አጠቃቀም ዕቅድ ይፋ ሆነ

104
አዲስ አበባ (ኢዜአ) የካቲት 13/2012  በጋምቤላ ክልል ይፋ የተደረገውን የተቀናጀ የመሬት አያያዝና አጠቃቀም አስመልክቶ ዛሬ በአዲስ አበባ ውይይት ተካሂዷል፡፡ የጋምቤላ ሕዝቦች ብሄራዊ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ታንኳይ ጃክ ውይይቱን ሲከፍቱ እንደተናገሩት፤ የተቀናጀ የገጠርና ከተማ መሬት አያያዝና አጠቃቀም ዕቅድ የአካባቢውን ማህበረሰብ ግንዛቤ በማሳደግ የተፈጥሮ ሃብቱን በባለቤትነት እንዲጠበቅ ያግዛል፡፡ ዕቅዱ የበካይ ጋዝ ተጠቂነትን ለመቀነስ ከፍተኛ ሚና እየተጫወተች የምትገኘው ኢትዮጵያ የአረንጓዴ ልማት ፖሊሲዎችን መሰረት አድርጋ የአካባቢና መሬት ጥበቃ ላይ በትኩረት ለመስራት መንገድ እንደሚከፍት ገልፀዋል፡፡ በክልሉ ያለው ለም መሬትና የተፈጥሮ ደን በአገሪቱ ለእርሻ ስራ ተመራጭ  በመሆኑ እቅዱ ተግባራዊ ሲደረግ በክልሉ ያለውን የእርሻና ተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ለማሻሻል ያስችላል ሲሉ ተናግረዋል፡፡ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሃና በበኩላቸው "በኢትዮጵያ በስፋት ስር ሰዶ ያለው የአካባቢ መራቆት ለደን መመናመን፣ ለአፈር መሸርሸር፣ ለምርት ማሽቆልቆልና ለድርቅ መፈራረቅ ቀዳሚውን ድርሻ ይወስዳል'' ብለዋል፡፡ ለዚህ ችግር ዋነኛው መንስኤ ዘላቂ የመሬት አያያዝና አጠቃቀም ዕቅድና ስርዓት አለመኖር መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡ ዕቅዱ በመሬት አያያዝና አጠቃቀም  ዙሪያ እያጋጠሙ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት ዓይነተኛ መሳሪያ እንደሚሆንም ተናግረዋል፡፡ የዕቅዱ ጥናት የተካሄደው በጋምቤላ ክልል ጥያቄ በግብርና ሚኒስቴር እና በአካባቢ፣ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን አስተባባሪነት ነው። በዚሁ መሰረት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ስር የሚገኘውና በአፍሪካ ቀንድ በሚገኙ ስድስት አገሮች የአካባቢ ጥበቃ፣ የብዝሃ-ህይወት፣ የተፈጥሮ ሃብት እንክብካቤ እና ዘላቂ ልማት ላይ እየሰራ የሚገኘው የአፍሪካ ቀንድ ማዕከል እና ኔትወርክ ተቋም እንደሆነ ታውቋል፡፡ በኢትዮጵያ የመጀመሪያ የሆነው የመሬት አያያዝና አጠቃቀም ዕቅድ ተግባራዊ ሲደረግ በክልሉ እያጋጠሙ ያሉትን የእርሻ መሬት ሽሚያ ያስቀራል ተብሎ ይገመታል። ዕቅዱ በሚቀጥሉት 20 ዓመታት በክልሉ ባሉ የተለያዩ ከተሞች፣ ዞኖችና ወረዳዎች ተግባራዊ ይደረጋል ተብሏል፡፡    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም