ባህላዊ የስፖርት ውድድር የንግድ ስራቸው እንዲነቃቃ ማገዙን በደብረማርቆስ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ

57

ደብረ ማርቆስ 13/06/2012 ሀገር አቀፉ ባህላዊ የስፖርት ውድድር የከተማዋን የንግድ እንቅስቃሴ ማነቃቃቱን  በከተማዋ አስተያየታቸውን  ነዋሪዎች ገለጹ። 17ኛው ሀገር አቀፍ የባህል ስፖርቶች ውድድር ከየካቲት 7/2012ዓ.ም. ጀምሮ በደብረ ማርቆስ ከተማ እየተካሄደ ይገኛል።

በከተማው የስለእናት መታሰቢያ ሆቴል ስራ አስኪያጅ አቶ በላይነህ ደጉ እንደገለፁት ውድድሩ በከተማዋ መካሄዱ የሆቴሉን የቀን ገቢያቸው እንዲጨምር ምቹ ሁኔታ ፈጥሮላቸዋል።

ከዚህ በፊት ከአካባቢው ነዋሪ በስተቀር ከሌላ ቦታ የሚመጡ እንግዶች ብዙም አያዘውትሩት  የነበረው ሆቴሉ ሰሞኑን ግን በርካታ እንግዶችን ማስተናገድ እንደቻለ ተናግረዋል።

ቀደም ሲል የሆቴሉ አልጋዎች ግማሽ ያህሉ ይከራዩ እንደነበር ጠቅሰው፤ አሁን ላይ ሁሉም ተይዘው አገልግሎት እየሰጡ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

ለእንግዶችም ከመደበኛው ክፍያ ቅናሽ በማድረግ እያስተናገዱ መሆናቸውንና ከዚህም የተሻለ ገቢ እያገኙ ስራቸው መነቃቃቱን አሰረድተዋል።

በጀበና ቡና የምትተዳደረው ወጣት ወለላ መንግስቴ በበኩሏ "በከተማዋ ስፖርት ወድድር መኖሩ የእለት ገቢየን እጥፍ ጨምሮልኛል" ብላለች።

ቀደም ሲል በቀን ከሁለት መቶ ብር የማይበልጥ የነበረው ሽያጭ  ሰሞኑን ስፖርታዊ ውድድሩ ከጀመረ ወዲህ የእለት ገቢዋ ከ500 ብር በላይ ማደጉን ገልፃለች።

በስፖርት ውድድሩ ምክንያት ቀደም ሲል በቀን ያገኘው የነበረው 100 ብር ሰሞኑን ከእጥፍ በላይ ማደግ እንደቻለ የተናገረው ደግ በጫማ  ማሳመር ስራ የተሰማራው ያለለት ምህረት ነው።

ደብረማርቆስ ሀገር አቀፉ ባህላዊ የስፖርት ውድድር ማስተናገዷ  የከተማዋን የንግድ እንቅስቃሴ እንዲነቃቃና ገቢያቸውን እንዲጨምር  ያገዛቸው መሆኑን አስተያየት ሰጪዎቹ ገልጸዋል።

የከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ አቶ ይትባረክ አወቀ እንዳሉት  ስፖርታዊ ውድድሩ የእርስ በእርስ ግንኙነትን ከማጠናከር ባለፈ የከተማዋን ገጽታ ለማስተዋወቅ እያገለገለ ነው።

በከተማዋ እየተከናወነ ባለው የባህል ስፖርት ውድድርም የከተማዋን ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ እንዲነቃቃ እድል ፈጥሯል ብለዋል።

በተለይም ቀደም ሲል በአካባቢው ተከስቶ በነበረው አለመረጋጋት ተቀዛቅዞ የነበረው የንግድ እንቅስቃሴ በማነቃቃት በተለያዩ የገቢ ማስገኛ የተሰማሩ ነዋሪዎች ገበያቸው እንዲሻሻል አግዟል።

"ሃገር አቀፉ  የባህል ስፖርት ውድድር ከሁለት ሺህ በላይ የልኡካን ቡድን ታዳሚ ሆነዋል" ያሉት ደግሞ የምስራቅ ጎጃም ዞን  ስፖርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ጌትነት ተስፋው ናቸው።

ውድድሩን በሰላማዊ ሁኔታ ጀምሮ ለማጠናቀቅና የተሻለ የሆቴልም ሆነ መሰል አገልግሎቶች እንዲቀርቡ ኮሚቴ ተቋቁሞ እየተሰራ እንደሚገኝ ተመልክቷል።

ነገ እንደሚጠናቀቅ በሚጠበቀው ሀገረ አቀፉ የባህል ስፖርት ውድድሩ ከትግራይ፣ አማራ፣ ቤንሻልጉል ጉምዝ፣ አፋር፣ ኦሮሚያ፣ ደቡብ ክልሎች እንዲሁም የድሬድዋ እና የአዲስ አባበ ከተማ አስተዳደሮች  የተወጣጡ ስፖርተኞችና የልኡካን ቡድን አባላት እየተሳተፉ መሆናቸውን በወቅቱ ዘግበናል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም