"ጥራት የሁሉም ስራችን መሰረት ሊሆን ይገባል" - ፕሬዚዳንት ሣሕለወርቅ ዘውዴ

84
አዲስ አበባ  የካቲት 13/2012 (ኢዜአ)  ጥራት የሁሉም ስራዎች መሰረት ሊሆን እንደሚገባ ፕሬዚዳንት ሣሕለወርቅ ዘውዴ ተናገሩ። 7ኛው ዙር የኢትዮጵያ ጥራት ሽልማት ድርጅት የሽልማት መርሃ ግብር ትናንት አመሻሽ በብሔራዊ ቤተ መንግስት ተካሂዷል። በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲና በዋልታ ሚዲያና ኮሙኒኬሽን ኮርፖሬት አማካኝነት ከ11 ዓመት በፊት የተቋቋመው የኢትዮጵያ ጥራት ሸልማት ድርጅት ዘንድሮ ለሰባተኛ ዙር 25 ድርጅቶችን አወዳድሯል። ድርጅትና ተቋማቱ በአምራች፣ በጤና፣ በትምህርት ተቋማት፣ በኮንስትራክሽንና የአገልግሎት ዘርፍ ሲሆኑ በዚህም ስምንት ድርጅቶች በተቀመጡ መስፈርቶች ተለይተው በሶስት ደረጃዎች ለሽልማት በቅተዋል። ሐረር ቢራና በባሕር ዳር ከተማ የሚገኘው ጋምቢ ጠቅላላ ሆስፒታል ደግሞ የአንደኛ ደረጃ የልህቀት ማዕረግ ዋንጫ ተሸላሚ ሆነዋል። ከስምንቱ ተሸላሚዎቹ መካከል ስድስቱ የማምረቻው ዘርፍ ሲሆኑ ሁለቱ ደግሞ የጤናና የአገልግሎት ዘርፍ ድርጅቶች ናቸው። በመርሃ ግብሩ ላይ ንግግር ያደረጉት የሽልማት ድርጅቱ የበላይ ጠባቂ ፕሬዚዳንት ሳሕለወርቅ ዘውዴ፤ "ጥራት የአስተሳስባችን ውጤት ነው፤ የሁሉም መሰረት ሊሆን ይገባል" ብለዋል። የጥራት ምስጢሩ "በጥራት ማምረት፣ ማገልገል፣ ማሳመርና መጭውን ትውልድ በጥራት መቅረጽ በመሆኑ በግዴታ ልንይዘው፣ ልናሳድገውና የሁሉም ስራችን መሰረት ሊሆን ይገባል" ብለዋል። ዘመኑ አዳዲስ ውጤት ፍለጋና ተፎካክሮ ለማሸነፍ ትግል የሚደረግበት በመሆኑ ድርጅቶች በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ ለመሆን የጥራትን አሰራር ሂደት መለማመድ እንደሚገባቸው አሳስበዋል። የጥራት ጉዳይ ተቋማዊ መሆን እንዳለበት የገለጹት ፕሬዚዳንቷ፤  "በምንሰራው ስራ ሁሉ ጥራት መንፀባረቅ አለበት" ብለዋል። የሽልማት ድርጅቱን አመስግነው ወደፊት የተሳታፊዎችን ቁጥር ማሳደግ፣ አደረጃጅቱን ማጠናከርና ጥቅሞችን ማስፋት ይጠበቅበታል ነው ያሉት። እንደ ድርጅቱ የበላይ ጠባቂም የሚቻላቸውን እንደሚያደርጉም ቃል ገብተዋል። የድርጅቱ የቦርድ ሰብሳቢና የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሃና በበኩላቸው፤ የአገሮች ውድድር እያደገ መምጣቱን ገልጸዋል። በዚህም ድርጅቶች ዘላቂነታቸውን ለማረጋገጥ በእያንዳንዱ ተግባራቸው ጥራትን ታሳቢ እንዲያደርጉ አስገንዝበዋል። በኢትዮጵያ ትርፋማና ተወዳዳሪ ለመሆን የሚጥሩ ድርጅቶች እንደሚያስፈልጉ ገልጸው፤ ''የሽልማት ድርጅቱም ጥራትን እያነቃቃ ነው'' ብለዋል። ድርጅቱ በየዓመቱ ከሚያደርገው አገር አቀፍ የጥራት ሽልማት ባሻገር ሌሎች ተጓዳኝ የመንግስት ተቋማትና ፕሮጀክቶች ልዩ የጥራት ሽልማት ለማካሄድ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል። ያም ሆኖ ድርጅቱ የተቋቋመበትን ዓላማና ግብ ለማሳካት የፋይናንስ ውስንነት እንዳለው ጠቅሰው፤ በሌሎች አገሮች ያሉ የሽልማት ድርጅቶች ከመንግስት የበጀት ድጋፍ እንደሚደረግላቸው ገልጸዋል። በዚህም መሰረት የኢትዮጵያ ጥራት ሽልማት ድርጅት ከመንግስት በጀት ተመድቦለት በገለልተኝነት እንዲሰራ ከሁለት ዓመት በፊት ረቂቅ ደንብ እንደተዘጋጀለት ተናግረዋል። ሆራይዞን አዲስ ጎማና መሰቦ ሲሚንቶ የግል ድርጅቶች የሁለተኛ ደረጃ የልህቀት ዋንጫ ሲሸለሙ፣ ሞግሌ የታሸገ ውሃ ማምረቻ ፋብሪካ፣ ማይጨው ፓርቲክልስ፣ ቡራዩ ልማትና ሳውዝ ስታር ሆቴል የሶስተኛ ደረጃ የልህቀት ዋንጫ ተበርክቶላቸዋል። የዘንድሮውን ሳይጨምር እስካሁን 349 ተቋማት እና ድርጅቶች ተወዳድረው 66ቱ የድርጅቱን የልህቀት ማዕረግ ዋንጫ አሸናፊ መሆናቸው ተወስቷል።፡፡    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም