በጠቅላይ ኢታማዦር ሹሙ የተመራ የልዑካን ቡድን በሳዑዲ ዓረቢያ የስራ ጉብኝት አደረገ

50
አዲስ  አበባ የካቲት 13/2012 (ኢዜአ) በጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጄኔራል አደም መሀመድ የተመራ የኢትዮጵያ ከፍተኛ የልዑካን ቡድን በሳዑዲ ዓረቢያ የስራ ጉብኝት አደረገ። የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሔራዊ ደህንነት አማካሪ ሚኒስትር ዴኤታ ተስፋሁን ጎበዛይ እንዲሁም የአገር መከላከያ ከፍተኛ አመራሮችን ያካተተው ከፍተኛ የልዑካን ቡድን ከየካቲት 12 እስከ 13 ቀን 2012 ዓ.ም በሳዑዲ ዓረቢያ ሪያድ የስራ ጉብኝት አድርጓል። የልዑካን ቡድኑ ከሳዑዲ ዓረቢያ ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጄኔራል ፈያድ ቢን ሃመድ አል-ሩዋሊና ከአገሪቷ የመከላከያ ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር በመገናኘት በሁለትዮሽና በቀጣናዊ የሠላምና ጸጥታ ጉዳዮች ዙሪያ ተወያይቷል። በውይይቱ በኢትዮጵያና በሳዑዲ የመከላከያ ዘርፍ ያለውን የሁለትዮሽ ትብብር ለማጠናከርና በሌሎች ቀጣናዊ የጋራ ስጋቶች ዙሪያ በትብብር መስራትና የልምድ ልውውጥ ማድረግ በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ ምክክርና የሃሳብ ልውውጦች ተደርገዋል። የልዑካን ቡድኑ በሪያድ የሚገኘውን እስላማዊ ጸረ-ሽብርተኝነት ወታደራዊ ጥምረት ማዕከል ዋና ጽህፈት ቤት በመጎብኘትም ከማዕከሉ አመራሮች ጋር ሽብርተኝነት በመከላከል ረገድ በጋራ መስራት በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ መክሯል። የሳዑዲ ዓረቢያ መንግስት ኢትዮጵያ በተባበሩት መንግስታት ድርጅትና በአፍሪካ ሕብረት የሠላም ማስከበር ተልዕኮዎች ተሳትፎ ለቀጣናው ሠላምና መረጋጋት እያበረከተች ያለውን አስተዋጽኦ እንደሚያደንቅና በዚህ ረገድ የበኩሉን ድጋፍ ለማድረግ ያለውን ዝግጁነት አረጋግጧል። የልዑካን ቡድኑ በሪያድ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ለዜጎች የሚሰጠውን የቆንስላ አገልግሎትም ጎብኝቷል። የልዑካን ቡድኑ በተጨማሪም በንጉስ ሳልማን የሰብዓዊ ዕርዳታ ማስተባበሪያ ማዕከል፣ በሳዑዲ ዓረቢያ የሹራ ምክር ቤት፣ በንጉስ አብዱልአዚዝ የታሪክ ማዕከልን መጎብኘቱን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት መረጃ ያሳያል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም