አየር መንገዱ የስካይላይት ሆቴሎችን በተለያዩ የአገሪቷ ክፍሎች ሊያስገነባ ነው

66
አዲስ አበባ (ኢዜአ) የካቲት 13/2012 የኢትዮጵያ አየር መንገድ የስካይላይት ሆቴል ቅርንጫፎችን በአገሪቷ የቱሪስት መዳረሻ ስፍራዎች ለማስገንባት በዝግጅት ላይ መሆኑን አሰታወቀ። በኢትዮጵያ ከከተሞች ራቅ ብለው በሚገኙ የቱሪስት መዳረሻዎቿ ደረጃቸውን የጠበቁ ሆቴሎች አለመኖራቸው ከዘርፉ የሚጠበቀውን ያህል ገቢ እንዳታገኝ አድርጓል። ደረጃቸውን የጠበቁ ሆቴሎች በበቂ አለመኖር የውጭ አገራት ጎብኚዎች የቆይታ ጊዜ እንዲያጥር በማድረጉ ከዘርፉ ሊገኝ የሚገባውን ሃብት እያሳጣ ስለመሆኑ ይገለጻል። የአየር መንገዱ የንግድ ዘርፍ ዋና ኃላፊ አቶ ኢሳያስ ወልደማሪያም ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የስካይላይት ቅርንጫፍ ሆቴሎችን በተለያዩ የአገሪቷ የቱሪስት መዳረሻዎች ለማስገንባት ዝግጅት እየተደረገ ነው። የእነዚህ ሆቴሎች መገንባት ወደ አገር ውስጥ የሚመጡ ቱሪስቶችን ቁጥር ለመጨመር ታሳቢ ተደርጎ እንደሆነም ጠቁመዋል። "የሚገነቡት ሆቴሎች ሙሉ በሙሉ ባለ አምስት ኮከብ ባይሆኑ እንኳ ደረጃቸውን የጠበቁ ሎጆች ሆነው ይገነባሉ" ያሉት አቶ ኢሳያስ ይህም ጎብኝዎች በቆይታቸው ደስተኞች እንዲሆኑ በማድረግ የቱሪዝም ዘርፉን ለማሳደግ እንደሚረዳ አመልክተዋል። ሆቴሎቹ በዳሎል፣ በኤርታሌ፣ በባሌ ተራሮች፣ በራስ ዳሽን፣ በአርባ ምንጭና በሌሎች የቱሪስት መዳረሻ ስፍራዎች እንደሚገነቡም አስታውቀዋል። የኢትዮጵያ አየር መንገድ እንደ አውሮጳዊያኑ አቆጣጠር በ2035 በዓለም ዙሪያ የቱሪስት ፍሰቱን ወደ 15 ሚሊዮን ለማሳደግና በሆቴሎች አገልግሎት የቱሪስቱን የቆይታ ጊዜ ያማረ ለማድረግ እየሰራ ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም