በትግራይ የአፈር ለምነት መጠን ጨምሯል-የምሁራን ጥናት

115
መቀሌ (ኢዜአ) የካቲት 13/2012 ዓ.ም በትግራይ ለዓመታት በተሰራው የተቀናጀ የአፈርና ውሃ ጥበቃ የክልሉን የአፈር ለምነት 53 በመቶ መጨመሩን የመቀሌ ዩኒቨርስቲ ምሁራን አስታወቁ። በትግራይ ካለፉት 30 ዓመታት ጀምሮ ሲካሄዱ የቆዩት የአካባቢ ጥበቃ ስራዎችና ያስገኙት ለውጦችን አስመልክተው ላለፉት አምስት ዓመታት የመቀሌ ዩኒቨርስቲ ምሁራን ሰፊ ጥናት አካሔደዋል። በጥናቱ ላይ ከተሳተፉት ምሁራን መካከል ፕሮፌሰር ምትኩ ሃይለ እንደሚሉት ምሁራኑ ለጥናታቸው መነሻ የተጠቀሙባቸው ከ140 ዓመት በፊት በሰሜን ኢትዮጵያ የነበረው የደን ሽፋን፣ የመሬት አጠቃቀምና የወንዞች የፍሰት መጠን ይጠቀሳሉ። በተጨማሪም ከ1868 ዓ.ም ጀምሮ እስከ አድዋ ጦርነት ድረስ የተነሱት ፎቶግራፎችና የሳተላይት ምስሎችን ከእንግሊዝና ጣሊያን በማስመጣት ምሁራኑ ለጥናታቸው ግብአቶች እንደተጠቀሙባቸው ነው ፕሮፌሰር ምትኩ የተናገሩት። ክልሉ ለዘመናት የጦርነት ቀጠና ሆኖ በመቆየቱ ለደን ሃብት መመናመን የነበረው አስተዋፅኦ እና ለዘመናት የቆየው የኋላቀር አስተራረስ ለአፈር መከላት ያደረገው አስተዋፅኦ በጥናቱ ውስጥ ተዳሷል። እንዲሁም ህብረተሰቡ ለማገዶና ለተለያዩ አገልግሎቶች የደን ውጤቶችን በስፋት መጠቀሙ ያስከተለው ተፅእኖ የጥናቱ አካል እንደነበርም ፕሮፌሰሩ ተናግረዋል። ከትጥቅ ትግሉ ጀምሮ በክልሉ ሲካሄድ የቆየው  የአፈርና ውሃ አጠቃቀምና የህዝቡ ተሳትፎ ለማጎልበት የተሰሩት ስራዎች፣ እየተመዘገቡ የመጡት ለውጦችን እንዲካተት ባደረገ መልኩ ጥናቱ በተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች መካሄዱን ፕሮፌሰር ምትኩ ተናግረዋል። ከ20 ዓመታት በፊት የአፈርና ውሃ ጥበቃ ያልተሰራለት ተዳፋት መሬት በክረምት ወቅት በሄክታር 420 ኩንታል አፈር በጎርፍ ይወሰድ እንደነበር ጥናቱ አመላክቷል። ባለፉት አመታት ተዳፋት መሬትን ማእከል በማድረግ የጥበቃ ስራዎች ሲከናወኑ በመቆየታቸው በተግባር የሚታዩ ለውጦች መመዝገባቸው ፕሮፌሰር ምትኩ ይገልጻሉ። የተቀናጀ የአፈርና ውሃ ጥበቃ የተሰራለት አካባቢ ከአንድ ሔክታር በአማካይ በጎርፍ የሚወሰደው የአፈር መጠን ወደ  170 ኩንታል  መውረዱን በጥናቱ ተረጋግጧል ። በትግራይ ማእከላዊ ዞን በቆላ ተምቤን ወረዳ በመረረ አካባቢ፣ በምስራቃዊ ዞን በክልተ አውላዕሎ ወረዳ በአብርሃ ወአፅብሃ አካባቢና በአጉላዕ ወረዳ በሓየሎም ቀበሌ አካባቢ የተሰሩት የጥበቃ ስራዎች በአብነት በመጥቀስ  ለውጦች እየታዩባቸው ነው ብለዋል። ከዚህ ቀደም የከርሰ ምድር ውሃን ለማግኘት በአማካይ እስከ 10 ሜትር ድረስ ጥልቀት ያለው ጉድጓድ መቆፈር የግድ ይል እንደነበር ጥናቱ አስረድቷል። ለአመታት በተካሄደው የተቀናጀ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ በየዓመቱ የሚዘንበው ዝናብ ወደ መሬት መስረግ በመቻሉ የከርሰ ምድር ውሃን ከ1 እስከ 3 ሜትር በሚደርስ ጥልቀት የሚገኝበት እድል መፈጠሩን አስረድተዋል ። የተቀናጀ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ የተካሔደባቸው አካባቢዎች የአፈር ለምነት እንዲጨምርና የከርሰ ምድር ውሃን እንዲጎለብት አስተዋፅኦ ማበርከቱን የተናገሩት ደግሞ  የጥናቱ ተሳታፊ የነበሩት ዶክተር ግርማይ ገብረ ሳሙኤል ናቸው። ስራው በተጠናከረ መልኩ በተካሔደባቸው አካባቢዎች የደን ሽፋን መጨመሩ፣በጎርፍ የሚወሰደው አፈር መቀነሱና የእፅዋትና የሳር ብስባሾች በመሬቱ ላይ እንዲቀሩ በማስቻል ለምነቱን እስከ 53 በመቶ እንዲጨምር ማድረጉን አስረድተዋል ። የጥበቃ ልማት ስራው በክረምት ወቅት የሚዘንበው ውኃ  በማሳና ተራራማ አከባቢዎች እንዲቀር እገዛ በማድረጉም ለአፈር ለምነት መጨመር ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ገልጸዋል። የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራውን ተከትሎ የከርሰ ምድር ውሃ መጎልበትና አመቱን ሙሉ የሚፈሱ ወንዞች በመፈጠራቸው ለመስኖ ልማት መስፋፋት ምቹ ሁኔታ እየፈጠሩ መምጣታቸውን በጥናቱ መረጋገጡን አስታውቀዋል። በቀጣይም የህዝቡን ጉልበት በአግባቡ በመጠቀምና በቴክኖሎጂ የታገዘ የእርከን ስራ በማካሔድ የአየር ንብረት ለውጥ ተፅእኖን ለመቀነስ የሚያግዝ በመሆኑ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ዶክተር ግርማይ አሳስበዋል። በክልሉ ግብርናና ገጠር ልማት ቢሮ የተፈጥሮ ሃብት ልማት ዳይሬክተር አቶ ክፍሎም አባዲ በበኩላቸው ከቻይናና ከተለያዩ አገራት ልምድ በመውሰድ ተፋሰሶችን መሰረት ያደረጉ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራዎች እየተካሄዱ መሆኑን ተናግረዋል። በትግራይ ክልል በየዓመቱ እስከ 70 ሺህ ሄክታር የሚሸፍን የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ እየተከናወነ መሆኑን ከአቶ ክፍሎም ገለፃ ለማወቅ ተችሏል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም