የጥራት ልህቀት ማዕረግ ሽልማቱ በዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪና ተደራሽ መሆን ያስችላል - ተሸላሚ ድርጅቶች

68
አዲስ አበባ (ኢዜአ) የካቲት 13/2012  የጥራት ልህቀት ማዕረግ ሽልማቱ በዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪና ተደራሽ ለመሆን እንደሚረዳቸው የ7ኛው ዙር የኢትዮጵያ ጥራት ሽልማት ድርጅት የልህቀት ዋንጫ አሸናፊዎች ተናገሩ። ድርጅቱ 7ኛውን ዙር የሽልማት መርሃ ግብር ትናንት ምሽት ሲያካሂድ ሐረር ቢራና ጋምቢ ጠቅላላ ሆስፒታል የአንደኛ ደረጃ የልህቀት ዋንጫ ወስደዋል። በተለያዩ ዘርፎች ከተወዳደሩ 25 ተቋማትና ድርጅቶች መካከል ስምንቱ ከአንደኛ እስከ ሶስተኛ ባሉት ደረጃዎች ተለይተው የልህቀት ዋንጫ ተበርክቶላቸዋል። በዚህም ሐረር ቢራና በባሕር ዳር የሚገኘው ጋምቢ ጠቅላላ ሆስፒታል የአንደኛ ደረጃ የልህቀት ማዕረግ ዋንጫ ተሸላሚ ሆነዋል። የሐረር ቢራ አክሲዮን ማኅበር የኢትዮጵያ ጥራት ሽልማት ድርጅት እስካሁን ባዘጋጃቸው ውድድሮች ለስድስት ጊዜ ተወዳድሮ በተደጋጋሚ የልህቀት ማዕረግ ዋንጫ ተበርክቶለታል። ዘንድሮም ለተከታታይ ሶስት ዓመታት የአንደኛ ደረጃ የልህቀት ዋንጫ በመውሰዱ ልዩ ተሸላሚ ሆኗል። የድርጅቱ ስራ አስኪያጅ አቶ ወንድወሰን ጥላሁን ለኢዜአ እንደገለጹት ድርጅቱ የጥራት ሽልማት ውድድሩን ማሸነፉ በምርት ጥራት፣ በደንበኞች ግንኙነት፣ በአካባቢ ጥበቃና ምርታማነት በአጠቃላይ አቅሙን ለማሻሻል እንዳገዘው ይገልጻሉ። በተመሳሳይ ሶስት ጊዜ ተወዳድሮ በሁለቱ የሶስተኛና ሁለተኛ ደረጃ፣ በዘንድሮው ውድድር ደግሞ የአንደኛ ደረጃ የልህቀት ዋንጫ ያሸነፈው የባሕር ዳሩ ጋምቢ ጠቅላላ ሆስፒታል ነው። የሆስፒታሉ ሜዲካል ዳይሬክተር ዶክተር ፈንታሁን አለሙ እንዳሉት ሽልማቱ ሆስፒታሉ ያሉበትን ክፍተቶች እየሞላ ጥራቱን የጠበቀ ተቋም እንዲሆን እንዳገዘው ተናግረዋል። ጋምቢ ከአገር ውስጥ የጥራት ሽልማት በተጨማሪ በሌሎች ዓለም አቀፍ የጥራት ሽልማት ውድድሮች በመሳተፍ የጎረቤት አገራት ደንበኞችን ለመሳብ እንቅስቃሴ ላይ መሆኑንም ገልጸዋል። ኃላፊዎቹ እንደሚሉት ጥራት የቅንጦት ሳይሆን ዘመኑ የሚጠይቀው የድርጅቶችን ህልውና የማስቀጠያ መስፈርት ነው። የኢትዮጵያ ጥራት ሽልማት ድርጅት መለኪያ መስፈርቶች ከሌሎች ዓለም አቀፍ መስፈርቶች ጋር ተመሳሳይ በመሆኑ ድርጅቶች በዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳደሪ እንዲሆኑ እንደሚያግዝም ነው የተናገሩት። በዚህም ሽልማቱ ድርጅቶች በምርትና አገልግሎታቸው ተወዳዳሪ፣ ተጠቃሚና ተደራሽ እንዲሆኑ እንዳስቻላቸው ተናግረዋል። በተጨማሪም የአገር ውስጥ ድርጅቶች ከውጭ በሚመጡ ሌሎች ተቋማት እንዳይዋጡና ዘላቂነት ያለው ስም ይዘው እንዲራመዱ የማድረግ ፋይዳ እንዳለውም አመልክተዋል። ሌሎች ያልተወዳደሩ ድርጅቶች በጥራት ተወዳድረው ራሳቸውን እንዲፈትሹም ጥሪ አቅርበዋል። የኢትዮጵያ ጥራት ሽልማት ድርጅት ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ቴዎድሮስ መብርሃቱ መሸለም ምንጊዜም ያበረታል፤ ወደተሻለ ደረጃም ይመራል ይላሉ። የጥራት ሽልማት ድርጅቶች እንደ ኮሪያና ጃፓን ምርቶች በዓለም አቀፍ ደረጃ ዕውቅ ሆነው እንዲዘልቁ የተጫወቱት ሚና ከፍተኛ መሆኑን ገልጸው ፤ የሚመሩት ድርጅት ዓላማም በኢትዮጵያ ይህን አጋጣሚ መፍጠር መሆኑን ተናግረዋል። ድርጅቶችና ተቋማት ምርትና አገልግሎቶቻቸው ተመዝነው እንዲበረቱና አገሪቷም በስሟ የሚጠራ ብራንድ እንዲፈጠር ያለመ ነው ብለዋል። 'ጥራት ዓለም አቀፍ ቋንቋ ነው' ያሉት አቶ ቴዎድሮስ ፤ ድርጅቱ የሚመራባቸው ዓለም አቀፍ መስፈርቶች በመሆናቸው ድርጅቶች ቢመዘኑ ለዘላቂነትና ትርፋማነት ፋይዳው የጎላ መሆኑን ገልጸዋል። ነገር ግን ድርጅቱ ካለበት የፋይናንስ እጥረት በተጨማሪ ለመወዳደር የሚመዘገቡ ድርጅቶችና ተቋማት ቁጥርም አናሳ መሆኑን ጠቅሰዋል። ይህም ከፍርሃትና ጥቅሙን ካለመገንዘብ የመነጨ እንደሆነ ገልጸው ፤ ድርጅቶች ፋይዳውን ተገንዘበው ስም የሚያስጠራ ተቋም በመመስረት ኢትዮጵያን ማስጠራት የሚችል ምርት እንዲያመርቱ ጠይቀዋል። በሌላ በኩል ማህበረሰቡ ለጥራት ያለውን ግንዛቤ አለማሳደግ አንዱ ችግር መሆኑን ጠቅሰው፤ በጥራት ያለመደራደር አመለካከት መገንባት አንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል። በ7ኛው ዙር ውድድር ሆራይዘን አዲስ ጎማና መሰቦ ሲሚንቶ የግል ድርጅቶች የሁለተኛ ደረጃ የልህቀት ዋንጫ ሲሸለሙ፤ ሞግሌ የታሸገ ውሃ ማምረቻ ፋብሪካ፣ ማይጨው ፓርቲክልስ፣ ቡራዩ ልማትና ሳውዝ ስታር ሆቴል የሶስተኛ ደረጃ ልህቀት ዋንጫ ተበክቶላቸዋል። የዘንድሮውን ሳይጨምር እስካሁን 349 ተቋማትና ድርጅቶች ተወዳድረው 66ቱ የድርጅቱን የልህቀት ማዕረግ ዋንጫ አሸናፊ መሆናቸው ተወስቷል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም