በመካነ ሰላም ከተማ በአንድ ቢለዮን ብር ወጪ የመጠጥ ውሃና መስኖ ልማት ፕሮጀክት ሊገነባ ነው

74
ደሴ (ኢዜአ) የካቲት 13/2012 ዓ.ም  በደቡብ ወሎ ዞን መካነ ሰላም ከተማ በአንድ ቢሊዮን ብር ወጪ ለመጠጥና መስኖ ልማት የሚውል ፕሮጀከት ግንባታ ለማስጀመር የቦታ ርክክብ ተካሄደ። የአማራ ክልል ውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ልማት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ መለስ ስንታዬሁ በትናንትናው ዕለት የግንባታ ቦታ ርክክብ ሲካሄድ እንደተናገሩት በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች የመጠጥ ውሃ ችግር ቢኖርም የመካነ ሰላም ከተማ ግን የከፋ ነው ብለዋል ። ችግሩን ለመፍታት የክልሉ መንግስት ጉዳዩን በልዩ ሁኔታ በመመልከት በአንድ ቢሊዮን ብር ወጪ ለንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦትና ለመስኖ ልማት የሚውል ግንባታ ለማካሄድ የዝግጅት ስራዎች ተጠናቋል ። የፕሮጀክቱን ግንባታ በሚቀጥለው ሳምንት  ለማስጀመር ለተቋራጩ ድርጅት ቦታውን ማስረከብ መቻሉን ጠቅሰዋል። ፕሮጀክቱ በቀጣይ ሁለት ዓመታት ግንባታው ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት ሲጀምርም 600 ሺህ ህዝብ የንጹህ መጠጥ ውሃ ተጠቃሚ ያደርጋል ። በተጨማሪም 409 ሔክታር መሬት በዘመናዊ መንገድ የመስኖ ልማት ለማካሔድ የሚያስችል መሆኑን አብራርተዋል። ግንባታው በተያዘለት ጊዜ በጥራት እንዲጠናቀቅ ክልሉ አስፈላጊውን እገዛና ክትትል ያደርጋል ያሉት ምክትል ኃላፊው ፤ ህብረተሰቡ ደንብ በማስከበርና ድጋፍ በማድረግ የድርሻውን እንዲወጣ ጠይቀዋል፡፡ 'አውስኮድ' የተሰኘው ተቋራጭ ስራ አስኪያጅ ተወካይ አቶ ከፍያለው ሙላቴ በበኩላቸው የፕሮጀክቱ ግንባታ በሚቀጥለው ሳምንት እንደሚጀመርና በተያዘለት ጊዜ ተጠናቆ ለአገልግሎት እንዲበቃ ለማድረግ የሚያስችል  ዝግጅት ተደርጓል ብለዋል። ፕሮጀክቱ በተያዘለት ጊዜ ተጠናቆ የህዝቡን የረጅም ጊዜ ጥያቄ ለመፍታት እንዲቻልም ህብረተሰቡ የበኩሉን እገዛ ማድረግ እንደሚገባው አቶ ከፍያለው ተናግረዋል ። የመካነ ሰላም ከተማ ውሃና ፍሳሽ አገልግሎት ጽህፈት ቤት ስራ አስኪያጅ አቶ ተስፋዬ ካሳ በበኩላቸው በከተማው የከርሰ ምድር ውሃ በቀላሉ አለመገኘቱ ህብረተሰቡ ለረጅም ጊዜ በንጹህ የመጠጥ ውሃ ችግር እንዲሰቃይ አድርጎታል ብለዋል፡፡ ችግሩ እንዲፈታ ተደጋጋሚ ጥያቄ ሲቀርብ መቆየቱን አውስተው ፤ አሁን ላይ የመጠጥ ውሃ አቅርቦቱን ከመፍታት ባለፈ ፕሮጀክቱ ለመስኖ ልማት ጭምር እንዲውል ተደርጎ እንዲገነባ የክልሉ መንግስት ያስቀመጠው አቅጣጫ በእጅጉ የሚያስመሰግን ነው ብለዋል። ፕሮጀክቱ በ12 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ወንዝ ተገድቦ በዘመናዊ መንገድ እየተጣራ ለህብረተሰቡ በቂ ውሃ እንዲደርስ የሚያደርግ መሆኑን ገልጸዋል። ግድቡ ከስድስት ሚሊዮን ሜትር ኩብ በላይ ውሃ የመያዝ አቅም እንዳለው ጠቅሰው ፤ ይህም የከተማዋን የወደፊት እድገት ታሳቢ ተደርጎ የሚገነባ መሆኑን አመልክተዋል። የመካነ ሰላም ከተማ ነዋሪ የሆኑት ወይዘሮ ገዛች ቸሩ በሰጡት አስተያየት በንጹህ መጠጥ ውሃ ችግር ለረጅም ዓመታት መሰቃየታቸውን አስታውሰው፤ ፕሮጀክቱ በተለይ የሴቶች ችግር ከመፍታት አንፃር ጠቀሜታው የላቀ ይሆናል የሚል ተስፋ ማሳደራቸውን ተናግረዋል ። በግንባታ ቦታው ርክክብ መርሃ ግብር ላይ የክልል፣ የዞን፣ የወረዳና የአካባቢው ነዋሪዎች ተገኝተዋል። በመካነ ሰላም ከተማ የንጹህ መጠጥ ውሃ ችግር አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን ኢዜአ በየካቲት ወር መግቢያ መዘገቡ ይታወሳል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም