የመድኃኒት የጎንዮሽና የአጠቃቀም ችግርን ለማቃለል ስድስት ማዕከላት መቋቋማቸው ተገለጸ

126
አዲስ አበባ፣ የካቲት 13/2012 (ኢዜአ) የመድኃኒቶች የጎንዮሽና የአጠቃቀም ችግርን ለማቃለል ስድስት ማዕከላትን ማቋቋሙን የኢትዮጵያ የምግብና መድሃኒት ባለስልጣን አስታወቀ፡፡ በባለስልጣኑ ቁጥጥር የሚደረግባቸው ምርቶች ደህንነት ዳይሬክተር ወይዘሮ አስናቀች ዓለሙ ለኢዜአ እንዳስታወቁት፤ በኢትዮጵያ ከመድኃኒት አጠቃቀም ጋር በተያያዘ የሚከሰቱ ችግሮችን ለመፍታት ጥረት እየተደረገ ነው። ከጥረቶቹ መካከል በተለያዩ አካባቢዎች የመድኃኒትን የጎንዮሽና የአጠቃቀም ችግርን ለማቃለል የሚሰሩ ማዕከላትን ማደራጀት ዋናው ተግባር ነው። በአዲስ አበባ፣ በጅማ፣ በሐረር፣ በሐዋሳ፣ በጎንደርና በመቀሌ በሚገኙ ሆስፒታሎች የተቋቋሙት ማዕከላት ከጥቅምት 2012 ጀምሮ  ሥራ መጀመራቸውን አስረድተዋል፡፡ እነዚህ ወደስራ የገቡ ማዕከላት መድሃኒት የሚወስዱ ሰዎች የሚያጋጥማቸውን የመድሃኒት የጎንዮሽ ጉዳት እንዲያሳውቁ የሚያስችሉና በመድሃኒት አወሳሰድ የሚያጋጥሙ ችግሮችን ለመፍታት እገዛ ያደርጋሉ። ማዕከላቱ ለችግሩ የሚሆን መፍትሄ የሚያቀርቡ እንደሆነም ገልጸዋል። ማዕከላቱ በኅብረተሰቡ ዘንድ የሚስተዋሉ የመድኃኒት አጠቃቀም ችግሮችን በዋነኝነት እንደሚያቃልሉ ገልጸዋል፡፡ ማዕከላቱ መድኃኒት ለሰው ልጅ ፈዋሽነት እንደሚያገለግሉ ሁሉ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ለአንዱ በሽታ የሚወሰዱ መድሃኒቶች የጎንዮሽ ጉዳት ሲያስከትሉ ይታያል፡፡ ''በርካታ መድሃኒቶች በተመረቱበት አገር ዜጎች ላይ ተሞክረው የተመረቱ ስለሆኑ አንዳንድ ጊዜ በእኛ አገር የጎንዮሽ ጉዳት ሲያሥከትሉ ይሥተዋላል'' ብለዋል፡፡ በተጨማሪም መድሃኒቶቹ በአቀማመጥ፣ በመጓጓዝ ሂደት ደህንነታቸው ያልተረጋገጠ ከሆነ የጎንዮሽ ጉዳት ሊያሥከትሉ እንደሚችሉ ዳይሬክተሯ ገልጸዋል፡፡ አንዳንድ ጊዜም መድሃኒቶች በተገቢው መንገድ ካልተወሰዱ የመላመድ ባህሪይ ስለሚኖራቸው ፈዋሽነታቸውን በማጣት የጎንዮሽ ጉዳት  ሊያሥከትሉ እንደሚችሉም ተናግረዋል፡፡ በአገር ውስጥ የሚመረቱ መድኃኒቶችም የጎንዮሽ ጉዳት እንዳያሥከትሉ ከምርት ጊዜ ጀምሮ ተጠቃሚው ዘንድ እስኪደርሱ ድረስ ደህንነታቸው ሊጠበቅላቸው ይገባልም ብለዋል፡፡ እነኚ ማዕከላት ከተቋቋሙ በኋላ 6 ሺህ 800 ጥቆማዎች ከህብረተሰቡ መድረሳቸውን ገልጸው መድሃኒቶቹም እንዲቀየሩና እንዲቀሩ ተደርገዋል ብለዋል፡፡ ከዚህ ቀደም የቲቢ እና የኤች አይ ቪ መድሃኒቶች ላይ በደረሰው ጥቆማ መሠረትና በተደረገው ጥናት እንዲቀየሩ መደረጋቸውን ዳይሬክተሯ አመልተዋል፡፡ በቀጣይም በሁሉም የአገሪቱ ክልሎች ሌሎች ማዕከላትን ለማቋቋም እየተሰራ እንደሚገኝም አመልክተዋል፡፡ በአገሪቱ ጥቅም ላይ እየዋሉ ከሚገኙ መድሃኒቶች 80 በመቶ የሚሆኑት ከውጪ ሀገራት የገቡ መሆናቸውን ከባለስልጣኑ የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡          
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም