በትግራይ የደን ልማትን ለማጠናከር 80 ሚሊዮን የዛፍ ችግኝ ተዘጋጀ

114
መቀሌ ሰኔ 20/2010 በትግራይ የደን ልማትን ለማጠናከር 80 ሚሊዮን ያህል የዛፍ ችግኝ በኩታገጠም ዘዴ ለተከላ መዘጋጀቱን የክልሉ ግብርናና ገጠር ልማት ቢሮ አስታወቀ። ችግኙ የሚተከሉት በክልሉ 36 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ መሆኑን በቢሮው የተፈጥሮ ሃብት ልማትና ጥበቃ ዳይሬክተር አቶ ክፍሎም አባዲ ለኢዜአ ገልጸዋል። በተለዩ የመንግስት ፣ የማህበረሰብና የግል የደን ስፍራዎች ላይ እንደሚተከል አመልክተው ለችግኙ የተከላ ቦታዎች ካርታ ተዘጋጅቷል፡፡ የሚተከለውም ከሰውና ከእንስሳት ነፃ በሆኑ፣በማይታረሱና ዳገት በበዛባቸው አካባቢዎች እንደሆነ ነው ዳይሬክተሩ የተናገሩት። ተከላ የሚካሄድባቸው ስፍራዎች እርጥበት እንዲቋጥሩ ለማድረግ የተለያዩ እርከኖች መገንባታቸውንም ጠቅሰዋል። "የተከላ ቦታዎቹ በተለያዩ ደረጃዎች ተከፋፍለው ለችግኞቹ የሚመች ርጥበት እንዲቋጥሩ በማድረግ በክልሉ የዝናብ ስርጭት ሲጀምር ወዲያውኑ በ15 ቀናት ውስጥ የተከላ ስራውን ይካሄዳል" ብለዋል። ከተከላ ስራ በተጓዳኝም  የደረቁት ዛፎችን በመለየት የመተካትና፣ የጸደቁትም በመኮትኮትና ውሃ በማጠጣት ህብረተሰቡ እንዲንከባከባው ይደረጋል። "ህብረተሰቡ ከአካባቢው ስነ ምህዳርና አፈር ጋር ተስማሚ የሆኑ ችግኞችን በመትከል እንዲያለማ ለማድርግም የመረጣቸው የችግኝ ዓይነቶች በነጻ እንደሚሰራጩ በማድረግ በባለቤትነት እንዲንከባከባቸው ይሰራል "ብለዋል። የችግኝ መትከል ስራው  የሰማእታት ቀንን ምክንያት በማድረግ ጭምር ነው። በክልሉ በየዓመቱ የችግኝ ተከላ እንደሚካሄድ ያስታወሱት አቶ ክፍሎም፣በዚህም የክልሉ የደን ሽፋን 14 መቶ መድረሱን አመልክተዋል።                      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም