ኔዘርላንድስ በኢትዮጵያ ያላትን ኢንቨስትመንት የማስፋት ፍላጎት አላት

49
አዲስ አበባ የካቲት 12/2020 ኔዘርላንድስ በኢትዮጵያ ያላትን ኢንቨስትመንት የማስፋት ፍላጎት እንዳላት የአገሪቷ የውጭ ንግድ እና የልማት ትብብር ሚኒስትር ሲግሪድ ካግ ገለፁ። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ዛሬ ማለዳ ከኔዘርላንድስ የውጭ ንግድ እና የልማት ትብብር ሚኒስትር ሲግሪድ ካግ ጋር በጽህፈት ቤታቸው ተወያይተዋል። ለረጅም ዘመናት የዘለቀ ወዳጅነት ያላቸው ሁለቱ አገሮች በተለያዩ መስኮች በትብብር ይሰራሉ። ባሳለፍነው የፈረንጆቹ አመት  የኔዘርላንድስ ንግስት ማክሲማ በኢትዮጵያ ጉብኝት ማድረጋቸውም ይታወሳል። ንግስቲቷ  በኢትዮጵያ በነበራቸው ቆይታ ኔዘርላንድስ ለኢትዮጵያ የፋይናንስ ስትራቴጂ ዕቅድ ድጋፍ እንደምታደርግ መግለፃቸውም እንዲሁ። ዛሬ ማለዳውን በኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ የተገኙት የኔዘርላንድስ የውጭ ንግድ እና የልማት ትብብር ሚኒስትር ሲግሪድ ካግ ተሰርቆ  ከኢትዮጵያ የወጣውንና በኔዘርላንድስ ውስጥ የተገኘውን የ18ኛው ክፍለ ዘመን የኢትዮጵያን ዘውድ አስረክበዋል። ከቅርስ ርክክቡ በኋላ በሁለቱ አገሮች የትብብር ግንኙነት ላይ ያተኮረ ውይይት ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ጋር አድርገዋል። ከውይይቱ በኋላ ሚኒስትሯ ሲግሪድ ካግ በሰጡት አስተያየት፤ ኔዘርላንድስ በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለውን የለውጥ ሂደት እንደምታደንቅና እንደምትደግፍ ገልፀዋል። ኔዘርላንድ በኢትዮጵያ ትልቅ ኢንቨስትመንት እንዳላት እና ይሄንኑ ወደ ላቀ ደረጃ የማሸጋገር ፍላጎት እንዳላትም ነው የተናገሩት። የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የፕሬስ ሴክረታሪያት ሃላፊ አቶ ንጉሱ ጥላሁን በበኩላቸው በርካታ የኔዘርላንድስ ባለሃብቶች በአንቨስትመንት መሰማራታቸውን ተናግረዋል። በተለይም በአበባ ልማት በስፋት ተሳትፎ እያደረጉ መሆናቸውን ገልጸው፤ ወደፊት ኢንቨስትመንቱን ለማስፋትና የንግድ ትብብሩን ማጠናከር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ምክክር መደረጉን ገልጸዋል።   ኢትዮጵያና ኔዘርላንድስ ከንግድና ኢንቨስትመንት ግንኙነታቸው ባለፈ በጤና፣ በግብርና እንዲሁም በትምህርት መስኮች በትብብር ይሰራሉ።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም