የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር በውጭ አገሮች የሚገኙ የኢትዮጵያን ቅርሶች ለማስመለስ እየሰራ ነው

44
አዲስ አበባ፣ የካቲት 12/2012(ኢዜአ) በተለያዩ ጊዜ በስርቆትና በተለያየ መንገድ ከአገር የወጡ የኢትዮጵያን ቅርሶች ለማስመለስ እየተሰራ እንደሆነ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር አስታወቀ። በ18ኛው ክፍለ ዘመን የነበረና በ1985 ዓ.ም እንደጠፋ የሚነገረው የኢትዮጵያ የዘውድ ቅርስ በኔዘርላንድስ ሮተርዳም ከተማ ተገኝቶ ዛሬ ለኢትዮጵያ መንግስት መመለሱ ይታወቃል። ይህን ተከትሎ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትሯ ዶክተር ሂሩት ካሳው ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ ዛሬ የተመለሰውን የዘውድ ቅርስ ጨምሮ ኢትዮጵያ በርካታ ቅርሶች በውጭ እንዳሏት አንስተዋል። የዘውዱ ቅርስ በተወሰደበት ዘመንና ቀን ሌሎች ሰባት ቅርሶች አብረው የተወሰዱ መሆኑን ያነሱት ሚኒስትሯ፤ ''ቀሪዎቹን ቅርሶችና በሌሎች አገሮች ያሉትንም ለማስመለስ በመንግስት በኩል በትኩረት እየተሰራበት ነው'' ብለዋል። ባህልና ቱሪዝም ከውጭ ጉዳይና ከሚመለከታቸው የአገሮች አምባሳደሮች ጋር በመሆኑን በተለይ ከእንግሊዝ ኤምባሲ ጋር በዚያ ያሉትን ቅርሶች የማስመለስ ስራ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል። ባለፈው አመትና ዘንድሮ ከእንግሊዝ የተመለሱ ቅርሶች መኖራቸውን በማስታወስ፣ በቅርብ ጊዜም ከዚያው ከእንግሊዝ አገር በቅርብ ቀን የሚመለሱ ቅርሶች አሉ ብለዋል። ''አዲስ አበባ ላይ ለሙዚየም የጠየቅነው  ቤት አለ'' ያሉት ሚኒስትሯ፤ ቤቱ ሲሰጥ ቅርሶቹ እንደሚመጡ አክለዋል። በእንግሊዝ ያሉትን በርካታ የኢትዮጵያ ቅርሶች የማስመለሱ ስራ የዓለም አቀፍ ህጉን ተከትሎ እየተሰራ ቢሆንም  ''የሙዚየም ህጋቸው ያጸደቀው ይህን ስለማይፈቅድ አስቸጋሪ ሆኗል'' ብለዋል። ይሁን እንጂ በእንግሊዝ ያሉትን ቅርሶች ላልተወሰነ ጊዜ በውስት እንዲመጣ መፈቀዱን ገልጸው፤ ''ቅርሶቹን በዘላቂነት ወደ አገር ማምጣቱ ላይ የመፍትሄ ሃሳቦች እየተፈለጉ ነው'' ብለዋል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም