የኢትጵያ ስካይላይት ሆቴል የባለ አምስት ኮከብ ሆቴልነት የብቃት ማረጋገጫ አገኘ

96
አዲስ አበባ የካቲት 12/2020  የኢትጵያ ስካይላይት ሆቴል የባለ አምስት ኮከብ ሆቴልነት የብቃት ማረጋገጫ ዛሬ ከባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ያገኘ ሲሆን ሌሎች ሶስት ሆቴሎችም  የአገልግሎት የጥራት ምደባ ተሰጥቷቸዋል። ዓለም አቀፍ የቱሪዝም ገበያን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማሳደግ የሆቴሎች የአገልግሎት ጥራት ወሳኝ መሆኑን የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር አስታወቀ። የደረጃ ምዘናና የአገልግሎት ብቃት ማረጋገጫ ምስክር ወረቀቱን የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዶክተር ሂሩት ካሳው ለሆቴሎቹ ባለቤቶችና ተወካዮች አበርክተዋል። ዶክተር ሂሩት ካሳው በወቅቱ ባደረጉት ንግግር ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለይ በመዲናዋ የሚገኙ ሆቴሎች ደረጃቸውን እያሻሻሉና ተወዳዳሪ እየሆኑ መምጣታቸውን አንስተዋል። ይህም  ዓለም አቀፍ የቱሪዝም ገበያ ውስጥ የተሻለ ቦታ ለማግኘት ደረጃቸውን የጠበቁ የአገልግሎት ሰጪ ተቋማት ማስፋት ወሳኝ እንደሆነና የአገር ውስጥም ሆነ የውጪውን የቱሪስት ፍሰት ለመጨመር ትልቅ መደላድል እንደሚፈጥር አንስተዋል። የኢትዮጵያ አየር መንገድ የንግድ ዘርፍ ዋና ሃላፊ አቶ ኢሳያስ ወልደማሪያም በበኩላቸው አየር መንገዱ ላለፉት በርካታ ዓመታት የኢትዮጵያን ቱሪዝም በተለያዩ መንገዶች ሲያስተዋውቅ የቆየ መሆኑን አስታውሰዋል። የስካይላይት ሆቴልም አገልግሎት መስጠት ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ በርካታ ቱሪስቶችን እያስተናገደ መሆኑን በመግለጽ፤ በቀጣይም ሆቴሉ የተሻለ አገልገሎት ለመስጠት ማስፋፊያዎችን እየሰራ እንደሆነ አንሰተዋል። ዛሬ በተሰጠው የደረጃ ምደባ ቤድሎት ሆቴል ባለአንድ ኮከብ፣ ቴዎድሮስ በላይ ኢንተርናሽናል ሆቴል ባለሁለት ኮከብ፣ ዴንቨር ሆቴል ባለ ሁለት ኮከብ፣ ስካይላይት ሆቴል ባለ አምስት ኮከብ ሆቴል የመሆናቸው ማረጋገጫ ተሰጥቷቸዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም