ባለስልጣኑ 5 ቢሊዮን ብር በሚጠጋ ወጪ አራት የመንገድ ፕሮጀክቶችን ሊያስገነባ ነው

66
አዲስ አበባ፣ የካቲት 12/2012 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን አራት የመንገድ ፕሮጀክቶችን 5 ቢሊዮን ብር በሚጠጋ ወጪ ለማስገንባት ከሥራ ተቋራጮች ጋር ተፈራረመ። የመንገድ ፕሮጀክቶቹ ከፍተኛ የህዝብ ጥያቄ ሲቀርብባቸው የነበሩ፣ ልማትን ለማሳለጥና የቱሪስት ፍሰቱን ለመጨመር የሚያግዙ ናቸው ተብሏል፡፡ የመንገዶቹን ግንባታ ለማካሄድ በባለስልጣኑ መሰብሰቢያ አዳራሽ ዛሬ የስምምነት ፊርማ ከተፈረመባቸው መንገዶች መካከል ከ1 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር በላይ የተመደበለትና ከ72 ኪሎ ሜትር በላይ ርዝመት ያለው የቆሼ-ሚቶ-ወራቤ ኮንክሪት የአስፋልት መንገድ አንዱ ነው። በተጨማሪም ከ1 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር በላይ የተመደበለት የጋምቤላ-አበቦ-ጎግ-ዲማ ሎት 72 ኪሎ ሜትር መንገድ ፕሮጀክት፣  ከ1 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር በላይ የተመደበለት የጊሸን መገንጠያ 14 ኪሎ ሜትር መንገድ እንዲሁም 10 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለውና የግንባታ ሥራው በ333 ሚሊዮን ብር የሚከናወነው የጎጂ ቆለላ ቆሬ አዲስ ዓለም መንገድ ፕሮጀክቶች ስምምነት የተደረገባቸው ናቸው። መንገዶቹ በሦስት አገር በቀል እና በአንድ የውጭ ኮንትራክተር የሚገነቡ ናቸው፡፡ የግንባታ ሥራውን የሚያከናውኑት አራቱ ሥራ ተቋራጮች ከኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ሀብታሙ ተገኝ ጋር ዛሬ ተፈራርመዋል፡፡ የመንገድ ፕሮጀክቶቹን በተያዘላቸው የጊዜ ገድብ ውስጥ በጥራት ሰርተው ለማስረከብ እንደሚንቀሳቀሱ የገለጹት ሥራ ተቋራጮቹ፤ የአካባቢው ማህበረሰብና የአስተዳደር አካላት ሥራው በወቅቱ እንዲጠናቀቅ ተገቢውን ትብብር እንዲያደርጉ ጠይቀዋል፡፡ የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ሀብታሙ ተገኝ ፕሮጀክቶቹ በመንግስት ከፍተኛ በጀት ተመድቦላቸው ወደሥራ የሚገቡ መሆናቸው ተናግረዋል። "ለመንገዶቹ ፈጥኖ መጠናቀቅ ባለስልጣኑ ከሚያደርገው የቅርብ ክትትል በተጨማሪ የየአካባቢው አስተዳደሮችም ሆኑ ሕብረተሰቡ ከፍተኛ ድጋፍ ሊያደርጉ ይገባል" ብለዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ በአካባቢያቸው በተገኙበት ወቅት ከህዝብ ለቀረበው ጥያቄ ፈጥኖ ምላሽ መሰጠቱ እንዳስደሰታቸው የተናገሩት ደግሞ በፊርማ ስነስርዓቱ ላይ የተገኙት የስልጤ ዞን አስተዳዳሪ አቶ አሊ ከድር ናቸው። የመንገድ ፕሮጀክቱ በተያዘለት ጊዜ ተጠናቆ ለህዝብ አገልግሎት እንዲበቃ አስተዳደሩ ከባለስልጣኑ፣ ከሥራ ተቋራጩና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እንደሚሰራም ቃል ገብተዋል፡፡ በስምምነቱ ላይ የተገኙት የሃይማኖት አባቶችና የአገር ሽማግሌዎችም የመንገድ ፕሮጀክቶቹ ጥራታቸውን ጠብቀው በተያዘላቸው የጊዜ ገደብ ውስጥ እንዲጠናቀቁ ተገቢውን ትኩረት እንዲሰጥ አስገንዝበዋል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም