በቴክኒክና ሙያ ትምህርት ስልጠና ላይ የጥራት ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችል እቅድና ፍኖተ ካርታ ተዘጋጀ

86
አዳማ፣ የካቲት 12/2012 (ኢዜአ) በቴክኒክና ሙያ ስልጠና ላይ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችል የቀጣይ አስር ዓመታት እቅድና ፍኖተ ካርታ መዘጋጀቱን የፌዴራል ቴክኒክና ሙያ ትምህርት ስልጠና ኤጄንሲ ገለጸ። የኤጀንሲው የ2012 በጀት ዓመት የመጀመሪያዎቹ ስድስት ወራት እቅድ አፈጻጻም ላይ የሚመክር መድረክ በአዳማ ከተማ እየተካሄደ ነው። በመድረኩ የኤጄንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው ነጋሽ እንደገለጹት የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ሥርዓት በተደራሽነት ላይ ውጤታማ ናቸው። ሆኖም በጥራት፣ እውቀትና ክህሎት የበቃ ውጤታማ የሰው ኃይል በማፍራት በኩል ሰፊ ክፍተት እንደሚታይባቸው አመልክተዋል። በዚህም ምክንያት በርካታ ወጣቶች ስልጠና ወስደው ወደ ሥራ መሰማራት እንዳልቻሉ ገልጸው ይህን ከመሰረቱ ለመቀየር የሚያስችል የቀጣይ አስር ዓመታት  እቅድ መዘጋጀቱን ተናግረዋል። ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ እድገትና ብልፅግናን ማረጋገጥ የሚችል ብቁ ዜጋን ለማፍራት የተዘጋጀው የዘርፉ ፍኖተ ካርታ ደግሞ ለ15 ዓመታት የሚቆይ ነው። እቅዱና ፍኖተ ካርታው የትምህርት ጥራት፣ሰልጣኞች የፈጠራና የአገልግሎት ባለቤት እንዲሆኑ፣ተደራሽነት፣የሥርዓተ ትምህርቱ ተገቢነትና ፍትሃዊነት ላይ ጥልቅ ጥናት በማካሄድና በምሁራን በማስተቸት የተዘጋጀ ነው። ይህም ሀገሪቱ የጀመረችውን የብልጽግና ጉዞ ለማሳካት በእውቀት፣ ክህሎትና መልካም ስነ ምግባር ታንጾ በራሱ የሚተማመን ዜጋ ማፍራት በማስፈለጉ ጭምር እንደሆነ ተጠቅሷል። የኤጄንሲው ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ኢሊያስ አወቀ በበኩላቸው "በራሱ የሥራ እድል መፍጠር፣ በጥቃቅንና አነስተኛ ኢንዱስትሪዎች መዋቅራዊ ለውጥ ማምጣት የሚችል የሰው ኃይል ያስፈልገናል" ብለዋል። ለዚህም በእቅዱ መሰረት ከ1ሺህ 620 በላይ የቴክኒክና ሙያ ትምህርት ስልጠና ኮሌጆችን ሥርዓተ ትምህርት ከመሰረቱ ለመለወጥ  እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል። ከዛሬ ጀምሮ ለሁለት ቀናት በሚካሄደው መድረኩ በኤጀንሲ የስራ አፈጻጸም፣ በእቅዱና ፍኖተ ካርታው ዙሪያ በመወያየት  ለተፈፃሚነት አጋዥ የሆኑ አቅጣጫዎች እንደሚቀመጡ ይጠበቃል።        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም