በቀወት ወረዳ አንድ ባለሀብት የ10 ኪሎ ሜትር የገጠር ጥርጊያ መንገድ አስገነቡ

70
ደብረብርሃን ሚያዝያ 25/2010 በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ቀወት ወረዳ በአንድ ባለሀብት የተገነባ የ10 ኪሎ ሜትር የገጠር ጥርጊያ መንገድ ለአገልግሎት በቃ፡፡ ከጭራ ሜዳ እስከ ማፉድ ቀበሌ ካሴ ሀገር ጎጥ የተገነባው ይሄው መንገድ ከሶስት ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ተደርጎበታል። የዞኑ አስተዳደር ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ክንፈ ሰይፉ በመንገድ ምርቃቱ እንደገለፁት  ባለሀብቱ ባልተለመደ ሁኔታ የመንገድ ግንባታ ማድረጋቸው ለህዝባቸውና ለአካባቢያቸው ልማት ያላቸውን ተቆርቋሪነት የሚያሳይ ነው። መንገዱ የአርሶ አደሩን ምርት በተሻለ ፍጥነት ወደ ገበያና የግብርና ገብዓቶችን በቀላሉ ወደ ለአምራቹ  ለማድረስ ያግዛል። "በቀጣይም ለአካባቢው ህዝብ የሚያገለግል መደበኛ የህዝብ ማመላለሻ ትራንስፖርት ይመደባል"ብለዋል ኃላፊው። የአካባቢው ተወላጅና  አሁን ደግሞ በአዳማ  ከተማ የሚኖሩት ባለሃብህቱ አርሶ አደሮች የመንገድ ችግሮቻቸው እንዲፈቱ በጠየቁት መሰረት ከአካባቢው አስተዳደር ጋር በመወያየት ግንባታውን ማከናወናቸውን ጠቁመዋል። ባለሀብቱ  ሀጂ አህመድ በሽር ኢብራሂም በበኩላቸው የአካባቢውን ነዋሪ ህዝብ የዘመናት የመንግድ ችግር በመመልከት ግንባታውን ማከናወናቸውን ገልጸዋል። ለመንገዱ ግንባታም ከሶስት ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ እንዳደረጉ ጠቁመው፤ የህዝቡን ችግር ለማቃለል ድጋፍ ማድረግ  በመቻላቸው ደስተኛ መሆናቸውንም ተናግረዋል። የአካባቢው አርሶ አደር ግርማ ጌታነህ በሰጡት አስተያየት ቀደም ሲል የተስተካከለ መንገድ ባለመኖሩ ወላድ እናቶች በቃሬዛ ለህክምና ሲወስዱ በመንገድ ላይ ህይወታቸዉ ያልፍ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ አሁን አምቡላንስ ወደ አካባቢው መግባት በመቻሉ ችግራቸው መቃለሉን አመልክተዋል፡፡ የመንገዱ መከፈት የህዝብና የጭነት ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች አገልግሎት መስጠት በመጀመራቸው የግብርና ምርቶቻቸውን አጓጉዘው ለተሻለ ገበያ ማቅረብ እንደሚያስችላቸው የገለጹት ደግሞ መርጌታ ግዛቸው ክፍሌ የተባሉ ነዋሪ ናቸው። የመኸር እርሻ ወቅት ከመድረሱም በፊት በተሽከርካሪ ምርጥ ዘርና ማዳበሪያ በወቅቱ እንዲያገኙ ምቹ ሁኔታ እንደፈጠረላቸውም ጠቅሰዋል፡፡ በቀጣይ መንገዱ ሲበላሽ ለጥገና የሚውል የአካባቢው አርሶ አደሮች 250 ሺህ ብር በማዋጣት በባንክ ማስቀመጥ መቻላቸውም ተመልክቷል። ባለሃብቱ ቀደም ሲል በሸዋ ሮቢት ከተማ 35ሚሊየን ብር በሆነ ወጪ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል በማስገንባት ለአካባቢውና ለአጎራባች ክልሎች ነዋሪዎች አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝም ተጠቅሷል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም