የኢንጂነር ስመኘው በቀለ መታሰቢያ ሐውልት ተመረቀ

60
አዲስ አበባ የካቲት 12/2012 ለቀድሞው የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዋና ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ስመኘው በቀለ የቆመው የመታሰቢያ ሐውልት ዛሬ ተመረቀ። በቅድስት ሥላሴ ካቴድራል የተገነባውን ሐውልት ያሰራው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ነው። የኢንጂነር ስመኘው ባለቤት እናት ወይዘሮ መንበረ መኮንን በምረቃው ሥነ ሥርዓት ላይ "ኢንጂነር ስመኘው ህይወቱ ቢያልፍም፡ የሥራው አሻራ አሁንም በህዳሴው ግድብ ግንባታ ላይ አለ" ብለዋል። የግድቡን ሠራተኞች ጨምሮ ዜጎች የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ለማጠናቀቅ ተረባርቦ በጋራ የመስራት ሃላፊነት እንዳለበት ገልጸዋል። መንግሥት ኢንጂነር ስመኘው ለግድቡ ግንባታ ላበረከቱት አስተዋጽኦ ለሰጠው እውቅናና ለቤተሰቦቹ እያደረገ ላለው ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበዋል። በጎንደር ማክሰኚት በ1957 ዓ.ም የተወለዱት ኢንጂነር ስመኘው በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ለረጅም ዓመታት አገልግለዋል። ከሥራዎቻቸውም ለሰባት ዓመታት የመሩት የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዋና ሥራ አስኪያጅነታቸው    በጉልህ የሚጠቀስ ነው። በተጨማሪም በግልገል ጊቤ አንድ የኃይድሮ ኤሌክትሪክ ማመንጫ ግድብ ፕሮጀክትን በምክትል ኃላፊነት፣ በግልገል ጊቤ ሁለት የኃይድሮ ኤሌክትሪክ ማመንጫ ግድብ ፕሮጀክትን በኃላፊነት መርተዋል። ኢንጂነር ስመኘው በ53 ዓመታቸው ሕይወታቸው ያለፈው ሐምሌ 19 ቀን 2010 ዓ.ም ነበር። ኢንጂነር ስመኘው የሶስት ልጆች አባት ነበሩ። በሐውልቱ ምረቃ ላይ የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ፣ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ዋና ስራ አስኪያጅ ኢንጂነር ክፍሌ ሆሮ፣ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ህዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ሮማን ገብረሥላሴና ሌሎች ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል። ኃላፊዎቹና የኢንጂነር ስመኘው ቤተሰቦች በሐውልቱ ሥር የአበባ ጉንጉን አኑረዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም