ወጣቶቸን ተጠቃሚ የሚያደርግ የቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎት የማስፋፊያ መርሃ ግብር ይፋ ሆነ

74
አዲስ አበባ፣ የካቲት 12/2012(ኢዜአ)አንድ ሚሊዮን ወጣት ጥንዶችን ተጠቃሚ ለማድረግ የሚያስችል የቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎት የማስፋፊያ መርሃ ግብር ይፋ ሆነ። ወጣቶች ላይ ትኩረት ያደረገው የቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎት ማስፋፊያ መርሀ ግብር በስድስት ክልሎች እንደሚተገበር ተገልጿል። ለመርሃ ግብሩ "የብልህ ጅምር ማስፋፊያ" የሚል ስያሜ የተሰጠው መሆኑም ታውቋል። የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ሊያ ታደሰ እንዳሉት መርሀ ግብሩ በተለይ ወጣቶች የቤተሰብ ምጣኔን ተግባራዊ እንዲያደርጉ ያግዛቸዋል። መርሃ ግብሩ ጥንዶች ልጅ የሚወልዱበትን ጊዜ፣ የሚወልዷቸውን ልጆች ብዛት እንዲሁም ለማሳደግ የሚያስፈልጋቸውን አዕምሯዊና የፋይናንስ አቅም ከግምት ውስጥ በማስገባት እንዲያቅዱ የሚያግዝ መሆኑንም ተናግረዋል። ወጣቶች ወደ ትዳር ከመግባታቸው በፊት እና ትዳር ከመሰረቱ በኋላ ሕይወታቸውን በዕውቀት እንዲመሩ የሚያስችል መሆኑንም አመልክተዋል። መርሃ ግብሩ ያለዕድሜ ጋብቻን ከመከላከል ባሻገር ያለዕድሜያቸው ወደ ትዳር የገቡ ሴቶች በዕቅድ በመውለድ  በጤናቸው፣ በትምህርትና በኢኮኖሚያቸው የተሻለ ደረጃ ላይ እንዲደርሱ ለማድረግ ያለመ መሆኑ ተመልክቷል። መርሃ ግብሩ በአውሮፓዊያኑ ከ2016 እስከ 2019 በኦሮሚያ፣ ትግራይ፣ አማራ እና ደቡብ ክልሎች በ36 ወረዳዎች ተግባራዊ ሆኖ ከ63 ሺህ በላይ ወጣት ሴቶችን ተደራሽ ማድረግ አስችሏል። የአሁኑ በማስፋፊያ መርሃ ግብርም ከ1 ሚሊዮን በላይ ወጣት ባለትዳሮችን ተደራሽ እንደሚያደርግ ይጠበቃል። የጤና ሚኒስቴር መርሀ ግብሩን በመደበኛ የጤና አገልግሎት ውስጥ በማካተት የቴክንከ ድጋፍ እንደሚያደርግ አስታውቋል። መርሃ ግብሩ ከፖፑሌሽን ሰርቪስ ኢንተርናሽናል ኢትዮጵያ፣ ከቻይልድ ኢንቨስትመንት ፈንድ ፋውንዴሽንና ቢል ኤንድ ሚሊንዳጌትስ ፋውንዴሽን በተገኘ 20 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ድጋፍ የሚተገበር መሆኑ ታውቋል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም