የምዕራብ አርሲ ዞንና የበደሌ ከተማ ነዋሪዎች የድጋፍ ሰልፍ አካሄዱ

69
አዳማ፣ የካቲት 12/2012 (ኢዜአ) የህዝቦች አንድነትና የብልጽግና ጉዞ እንዲጠናከር የሚደግፉ መሆናቸውን የምዕራብ አርሲ ዞንና የበደሌ ከተማ ነዋሪዎች ዛሬ ባካሄዱት ሰልፍ ገለጹ። በምዕራብ አርሲ ዞን ከሚገኙ ወረዳዎችና ከተማ አስተዳደሮች የተውጣጡ ነዋሪዎች ድጋፋቸውን የገለጹት በሻሸመኔ ከተማ ባካሄዱት ሰልፍ  የተለያዩ መፈክሮችን በማሰማት ነው። "ጅምራችን መደመር መዳረሻችን ብልፅግና፣ መጪው ጊዜያችን ከብልፅግና ጋር ብሩህ ነው፣ ከብልፅግና ጎን ቆመን ሀገሪቱን እናሻግራለን" የሚሉ ካሰሟቸው መፈክሮች ውስጥ ይገኙበታል። የጠቅላይ ሚኒስቴር ዶክተር አብይ አህመድ መደመር ለሀገር ሰላም፣ልማትና ዴሞክራሲ ብቸኛ አማራጭ መሆኑን አመልክተዋል። በዓለም ደረጃ የሰላምና የፍቅር አባት በመሆናቸው ራዕያቸውን ለማሳካት ድጋፋቸውን እንደሚያጠናክሩም ገልጸዋል። የምዕራብ አርሲ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዳስታ ነጌሶ  ለውጡን ለማስቀጠልና ሀገሪቱን ለማሻገር ህብረተሰቡ በአንድነት ከብልፅግና ጎን እንዲቆም  ጠይቀዋል። "የህዝቦችን አንድነት በማጠናከር ሀገራዊ ለውጡ ግቡን እንዲመታ የዞኑ ህብረተሰብ ማጋዝ ይጠበቅበታል" ብለዋል። "ሻሸመኔ ሁሉም ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች በመቻቻልና በመተሳሰብ አብረው በፍቅር የሚኖሩበት ከተማ ናት" ያሉት ደግሞ  የሻሸመኔ ከተማ ከንቲባ አቶ ተማም ሁሴን ናቸው። የከተማው ነዋሪ ህዝብ አንድነቱን ይበልጥ አጠናክሮ ለብልፅግናው ጉዞ መሳካት ድጋፉን መቀጠል እንዳለበትም አመልክተዋል። በድጋፍ ሰልፉ ለውጡን ለማገዝ  ከ20 በላይ ሰንጋዎችና ጥሬ ገንዘብ በህብረተሰቡ ድጋፍ ተደርጓል። ይህ በእንዲህ እንዳለ በቡኖ በደሌ ዞን የበደሌ ከተማና አካባቢው ነዋሪዎች ባካሄዱት ሰልፍ የህዝቡ አንድነትና የብልጽግና ጉዞ ለማጠናከር እንደሚደግፉ ገልጸዋል። ነዋሪዎቹ "ከብልፅግና ጋር መጪው ግዜ ብሩህ ነው! በሀገር ውስጥና በጎረቤት ሀገራት ለውጥ እያመጣ ካለ መሪ ጎን እንቆማለን" የሚሉ መፈክሮችንም አሰምተዋል። ከሰልፉ ተሳታፊዎች መካከል አቶ ተስፋዬ ልግዲ በሰጡት አስተያየት ብልጽግና  ከዚህ ቀደም የዳር ተመልካች የነበሩ ፓርቲዎችን በማቀፉ ለእውነተኛ ፌዴራሊዝም መረጋገጥ መቆሙን እንደተረዱ ተናግረዋል። "ጠቅላይ ሚንስትሩ በአለም አቀፍ ዲፕሎማሲ ሀገሪቱ ክብሯ ከፍ እንዲል አድርገዋል" ያሉት አስተያየት ሰጪው እንደ አንድ ዜጋ ኢትዮጵያ  ወደ አዲስ ምዕራፍ እንድትሸጋገር ድጋፋቸውን እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል። ህዝብን በአካባቢ ለይተው ለመከፋፈል ሲሞክሩ የብልፅግና ፓርቲ በሰከነ መንገድ አንድነት ለማጠናከር እየሰራ ያለው ለድጋፍ መነሳሳቱን የተናገረው ደግሞ ወጣት  ኬኔሳ ቦጂአ  ነው። የበደሌ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ይደነቃል ገዛኸኝ አዲሱ የብልፅግና ጉዞ ከመከፋፈል ይልቅ በመደመር የበለፀገች ሀገር መገንባት እንደሆነ አብራርተዋል። የቡኖ በደሌ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ ወይዘሮ ሊዲያ ጫሊ ህብረተሰቡ የጀመረውን ድጋፍ በማጠናከር ለሀገር ግንባታው የሚጠበቅበትን እንዲወጣ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል። በበደሌ ከተማ ዛሬ በተካሄደው የድጋፍ ሰልፍ  ሴቶች፣ ወጣቶች እና ሌሎችም የህብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፈዋል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም