ኢትዮጵያ ለቡና ምርቷ አዳዲስ የገበያ መዳራሻዎችን እያገኘች ነው

150
የካቲት 12 / 2012 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ስፔሻሊቲ የቡና ምርት በአሜሪካ፣ ቻይና ጃፓን እና የተለያዩ የአውሮፓ አገራት ተፈላጊነቱ እየጨመረ መሆኑን የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን አስታወቀ። የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክትር ዶክተር አዱኛ ደበላ ለኢዜአ እንድገለጹት የኢትዮጵያ ስፔሻሊቲ ቡና በተለያዩ የዓለም አገራት ተፈላጊነቱ እየጨመረ መጥቷል። ለዚህ የቡና ምርት በተለይም አሜሪካ፣ ቻይና፣ ጃፓን፣ ደቡብ ኮሪያ እንዲሁም የተለያዩ የአውሮፓ አገሮች ከፍተኛ ፍላጎት አሳይተዋል። በመሆኑም በአሜሪካ፣ ቻይና እንዲሁም በአውሮፓ በቡና ገበያ ተወዳዳሪ ሆኖ ለመቅረብ የስፔሻሊቲ ቡና ምርትን በስፋትና በጥራት ማቅረብ ይገባልም ነው ያሉት። ኢትዮጵያ አዲስ እየተገበራችው ባለችው የቡና ምርት ሪፎርም በስፔሻሊቲ ቡና ላይ ትኩረት አድርጋ  እየሰራች ትገኛለች። "ስፔሻሊቲ ቡና" የሚባለው ከለቀማ እስከ ማጠብ እንዲሁም አስተሻሸግ ጥራቱንና ቃናውን ጠብቆ ለገበያ በማቅረብ ሂደት ያለፈ ማለት ነው። ይህ የቡና አመራራት ዘዴ ቀደም ሲል በብራዚልና ኮሎቢያ በስፋት ሲተገበር የቆየና አሁንም የቀጠለ መሆኑ ይነገራል። አርሶ አደሩ የቡና የምርት ጥራቱን ጠብቆ እዲያምርት ለማስቻል ከዝግጅት እስከ አቅርቦት ያለውን ሂደት በባለሙያዎች ክትትልና ድጋፍ የታገዘ ማድረግ ይገባል ያሉት ዶክተር አዱኛ ከስፔሻሊቲ ቡና በተጫማሪ የሌሎች ምረቶችንም ጥራት ማስጠበቅ ይገባል ብለዋል። ከአሁን ቀደም ኢትዮጰያ ስትጠቀምበት የነበረውን የጨረታ ንግድ አሰራር ወደ ዘመናዊ በማድረግ ከአገራት ጋር በቀጥታ በመደራደር  ለመሸጥ እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል ። ኢትዮጵያ በዘንድሮው ዓመት 295 ሺህ ቶን ቡና ለውጭ ገበያ ለማቅረብ አቅዳ እየሰራች ትገኛለች።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም