ከ80 በላይ የምግብና የመድሃኒት አምራች እና አስመጪ ድርጅቶች ህጋዊ እርምጃ ተወሰደባቸው

56
አዲስ አበባ የካቲት 12/2012 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ የምግብና መድሃኒት ባለስልጣን በ84 የምግብና የመድሃኒት አምራችና አስመጪ ድርጅቶች ላይ ህጋዊ እርምጃ መውሰዱን አስታወቀ፡፡ ባለስልጣኑ የበጀት ዓመቱን የስድስት ወራት የስራ አፈጻጸም አስመልክቶ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል።፡ የባለስልጣኑ የሕዝብ ግንኙነትና ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ሳምሶን አብርሃም በዚሁ ጊዜ እንዳሉት ህገ-ወጥ ተግባራት ሲያከናውኑ በተገኙ ድርጅቶችና ተቋማት ላይ እርምጃ ተወስዷል፡፡ እርምጃ ከተወሰደባቸው መካከል 43 ድርጅቶች የተበላሹና የመጠቀሚያ ጊዜ ያለፈባቸውን ምግቦች ሲሸጡ የተገኙ ናቸው። ህገ-ወጥ መድሃኒቶችን ሲሸጡ የነበሩ እንዲሁም ተመሳስለው የተሰሩ መድሃኒቶች በድርጅታቸው የተገኙባቸው 41 ድርጅቶችም እርምጃ ተወስዶባቸዋል። በመሆኑም በእነዚህ ተቋማት ላይ ከጊዜያዊ እገዳ ጀምሮ የብቃት ማረጋገጫቸውን እስከመሰረዝ የሚደርስ እርምጃ የተወሰደባቸው መሆኑን አቶ ሳምሶን ገልጸዋል። በቁጥጥር ሂደቱ የተገኙ የተበላሹና ጊዜ ያለፈባቸውን ምግቦችን የማስወገድ ስራ መከናወኑን የገለጹት ዳይሬክተሩ ህገ-ወጥ መድሃኒቶችም ከገበያ እንዲሰበሰቡ ተደርጓል ብለዋል። በአገሪቱ መውጫና መግቢያ በሮች በተደረገ ቁጥጥር ከ4 ሚሊየን ብር በላይ ግምት ያላቸው የተለያዩ ህገ ወጥ መድሃኒቶች እንዲሁም ከ6 ሺህ 590 ቶን በላይ የተበላሹ ምግቦች እንዲወገዱ ተደርጓል። የኢትዮጵያ የምግብና መድሃኒት ባለስልጣን ከኅብረተሰቡ በሚያገኛቸው ጥቆማዎችና በሚያደርጋቸው ክትትሎች በህገ ወጦች ላይ የሚወስደውን ህጋዊ እርምጃ አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም