በቃርያ ላይ የተከሰተው በሽታ በገቢያቸው ላይ ተፅእኖ ማሳደሩን አርሶ አደሮች ገለፁ

152
ማይጨው፣ የካቲት 12/2012 (ኢዜአ) በትግራይ ክልል በአምራችነቱ በሚታወቀው ደቡባዊ ዞን ራያ ዓዘቦ ወረዳ በቃሪያ ላይ የተከሰተው በሽታ በምርታማነትና ገቢ ላይ ተፅእኖ ማሳደሩን አርሶ አደሮች ገለፁ። ባለፈው አመት በአካባቢው 48 ሺህ 800 ኩንታል ቃሪያ ተመርቶ የነበረ ቢሆንም ዘንድሮ በበሽታው ምክንያት ምርቱ በእጅጉ መቀነሱን አርሶ አደሮችና ባለሙያዎች ተናግረዋል። በራያ አዘቦ ወረዳ የካራ ቀበሌ ገበሬ ማህበር ነዋሪ አርሶ አደር ሱሌማን ጣሂር እንደገለፁት ''በበሽታው ምክንያት  ለቃርያ ብዬ ያዘጋጀሁትን ግማሽ ጥማድ መሬት በቀይ ሽንጉርት ለመተካት ተገድጃለሁ" ብለዋል። በበሽታው ምክንያት መሬቱ እየቀያየሩ ከማልማት የገታቸው ከመሆኑ ባሻገር ከቃሪያ ያገኙት የነበረው ምርትና ገቢ እንዲቀንስ ያደረጋቸው መሆኑን አስረድተዋል። ሌላኛው የዚህ ቀበሌ ነዋሪ ሴት አርሶ አደር  ኪሮስ ጥዑማይ በበኩላቸው ባለፈው አመት በሄክታር እስከ 300 ኩንታል ምርት የሚሰጥ "ሰረናዲ" ተብሎ የሚታወቅ የቃሪያ ዝሪያ በማልማት ተጠቃሚ እንደነበሩ ተናግረዋል። ዘንድሮ ግን በተወሰነ መሬት ላይ ቃሪያ ማልማት ጀምረው የነበሩ ቢሆንም ማፍራት ከመጀመሩ በፊት በበሽታው መጥፋቱን ገልጸዋል። የራያ አዘቦ ወረዳ  ግብርናና ገጠር ልማት ጽህፈት ቤት በቃርያ  ላይ በተከሰተ በሽታ ምክንያት በመስኖ ይለማ የነበረው የቃርያ ልማት ሽፋን እየቀነሰ መጥቷል ብሏል። የፅህፈት ቤቱ ሓላፊ አቶ መልአኩ ግርማይ ለኢዜአ እንደተናገሩት በወረዳው በ72 ጥልቅ ጉድጓዶች በመስኖ የሚለማ 5 ሺህ 800 ሄክታር መሬት መኖሩን ተናግረዋል። በወረዳው በብዛት ከሚለሙ አትክልቶች መካከል አንዱ ቃርያ  ቢሆንም አሁን በተከሰተው በሽታ ምክንያት ሽፉኑ ቀንሷል። ባለፈው አመት ከ390  ሄክታር መሬት በላይ በቃርያ ተሸፍኖ  እንደነበር ጠቅሰው ዘንድሮ ግን በበሽታው ምክንያት ሽፋኑ ወደ 290 ሄክታር ዝቅ ማለቱን አስረድተዋል። የአላማጣ ግብርና ምርምር ማዕከል ዳይሬክተር አቶ ክፍሎም ደገፍ በበኩላቸው በቃርያ ላይ የተከሰተው በሽታ ለማጥፋት የምርምር ስራዎች መጀመራቸውን ተናግረዋል። በቲማቲም እና በቃርያ ፍራፍሬዎች ላይ በተደጋጋሚ ጊዜ በሽታዎች ይከሰታሉ ያሉት ዳሬክተሩ ቲማቲም የሚያጠቃውን በሽታ መከላከል የተቻለ ቢሆንም የቃርያውን ግን አዲስ በመሆኑ እስከ አሁን ድረስ መፍትሔ አልተገኘለትም ብለዋል። በሽታው አርሶ አደሮችን ከቃርያ ምርት ውጪ እያደረጋቸው በመሆኑ ማዕከሉ ችግሩን ለመፍታት እየሰራ መሆኑን ገልፀዋል።        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም