በለቅሶ ላይ በተተኮሰ ጥይት የአንድ ግለሰብ ህይወት አለፈ

50
ባህርዳር ኢዜአ የካቲት 11/ 2012፡- በባህር ዳር ከተማ በለቅሶ ላይ የተተኮሰ ጥይት የሌላ ሰው ህይወት ማጥፋቱን ፖሊስ አስታወቀ። ለቅሶ  የነበረውም በተመሳሳይ በጥይት ህይወቱ ላለፈው ሰው ነው። በከተማ አስተዳደሩ የሶስተኛ ዋና ፖሊስ ጣቢያ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ዋና ኢንስፔክተር አብርሃም ልየው ለኢዜአ እንደገለጹት ድርጊቱ የተፈፀመው ትናንት አመሻሽ ላይ ወራሚት ተብሎ በሚጠራው ቀበሌ ነው። ድርጊቱም  አንድ ግለሰብ በዚሁ ዕለት ከምሽቱ ሁለት ሰዓት ተኩል አካባቢ በመጠጥ ስሜት ተገፋፍተው በታጠቁት የጦር መሳሪያ ራሳቸውን ሊያጠፋ እንደቻሉ ፖሊስ ባደረገው ማጣራት መረጋገጡን ተናግረዋል። የአካባቢው ነዋሪዎች የተኩስ ድምፅ ሰምቶ ሲወጣ የግለሰቡ ህይወት ማለፉን ሲመለከቱ በታጠቁት የጦር መሳሪያ ከተጎጂው ቤት ተደጋጋሚ ጥይት ይተኮሳል። የጥይት ተኩሱን የአካባቢ ምድብተኛ ፖሊሶች እንዲያስቆሙ በወቅቱ ጥረት ቢያደርጉም  ከአቅም በላይ በመሆኑ ድርጊቱን መግታት አለመቻሉን አስረድተዋል። ይተኮስ የነበረ ጥይት የሟች ጎረቤትና የቅርብ ጓደኛ የሆኑ ግለሰብን በመምታት ህይወቱ  ማለፉን ዋና ኢንስፔክተር አብርሃም አብራርተዋል። ድርጊቱን ፈፅሟል የተባለው ግለሰብም እስካሁን በቁጥጥር ስር ባለመዋሉ ይዞ ለፍርድ ለማቅረብ የአካባቢው የፀጥታ ኃይል የተጠናከረ የክትትል ስራ እያደረገ ይገኛል ብለዋል። ህብረተሰቡ የአካባቢውን ፀጥታ እንዲጠብቅ ታስቦ በቅርቡ የጦር መሳሪያ ፈቃድ የተሰጠ ቢሆንም መሰል ድርጊቶች እንዲበራከቱ ሰፊ እድል መፍጠሩን  ገልጸዋል። በቅርቡ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፀደቀው የጦር መሳሪያ አስተዳደርና ቁጥጥር አዋጅ አፈፃፀም ወደታች ሲወርድ ችግሩ በዘላቂነት ሊፈታ ይችላል የሚል እምነት እንዳላቸውም ተናግረዋል። የሟቾቹ የቀብር ሰነሰርዓት በየአካባቢያቸው  በሚገኙ ቤተክርስቲያናት ዛሬ መፈጸሙን  ዋና ኢንስፔክተሩ አመልክተዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም