ኢትዮጵያ ባለፉት ስድስት ወራት ወደ መካከለኛ የብድር ጫና ስጋት ቀነሰች

118
አዲስ አበባ፤ የካቲት 11/2012 ኢትዮጵያ ባለፉት ስድስት ወራት ያለባት የብድር ጫና ከከፍተኛ ወደ መካከለኛ ስጋት ማውረድ መቻሏን የገንዘብ ሚኒስቴር አስታወቀ። ሚኒስቴሩ በ2012 የበጀት ዓመቱን ስድስት ወራት ከበይነ መንግስታዊ ተቋማት (መልቲ ላተራል)  እና ከመንግስታት ሁለትዮሽ (ባይላተራል) የትብብር ምንጮች የተገኘውን ሃብት በሚመለከት ጋዜጣዊ መግለጫ ተሰቷል። በመግለጫውም ባለፉት ስድስት ወራት የአገሪቱ የውጪና የውስጥ ብድር ጫና እየቀነሰ በመምጣቱ፤ የብድር ጫናውን ከከፍተኛ ወደ መካከለኛ ስጋት ወርዷል ብሏል። አገሪቱ ለበርካታ የልማት ተግባራት ከታክስና ከሌሎች ገቢዎች ከምትሰበስበው ባሻገር ከውጪና ከአገር ውስጥ በብድር መልክ ከሚገኝ ገንዘብ የበጀት ጉድለቷን እንደምታሟላ ይታወቃል። የሚኒስቴሩ የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ሀጂ ኢብሳ እንደገለጹት በተጠቀሱት ወራት የማዕከላዊ መንግስት የአገር ውስጥ ብድር 12 ነጥብ 2 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ሲሆን የውጪ አገር ብድር ደግሞ 16 ነጥብ 7 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ነው። በአጠቃላይ የማዕከላዊ መንግስት ከአገር ውስጥ እና ከውጪ ተደምሮ ከ29 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር በላይ ብድር አለበት ብለዋል። ከብድር ጫና ጋር ተያይዞ አለማቀፉ የገንዘብ ተቋም / የአይ. ኤም. ኤፍ/ እና የአለም ባንክ ዘንድሮ ባካሔዱት የብድር ጫና ትንተና፤ ኢትዮጵያ ያለባት የብድር ጫና እየቀነሰ መምጣቱን አስረድተዋል። በመሆኑም ኢትዮጵያ በብድር ጫና ከነበረችበት ከፍተኛ ስጋት በመውጣት አሁን ላይ ወደ መካከለኛ ስጋት መሸጋገሯን ጠቅሰዋል። ለዚህ ማሻሻያ ምክንያት የሆነውም የቻይና የንግድ አበዳሪዎች የዕዳ ክፍያ ጊዜ ሽግሽግ እንዲራዘም በመደረጉ መሆኑን አመልክተዋል። የቻይና የእዳ ክፍያ ጊዜ ሽግሽግ እንዲራዘም መደረጉ በተለይም በባቡር ከ5 እስከ 10 ዓመት የእፎይታ ጊዜ የሚሰጥ መሆኑን አብራርተዋል። የቻይና ዋና እዳ ክፍያውንም በተመለከተ ከ10 እስከ 20 ዓመት እንዲራዘም መደረጉ የአገሪቱን የውጭ ምንዛሪ ጫና ለመታደግ መቻሉን አመላክተዋል። በሌላ በኩል ደግሞ አዲሱ የብድር መመሪያ ጥናትና የአዋጭነት ሁኔታዎች ታይተው ወደ ብድር የሚገባ መሆኑም አስተዋፆ አበረክቷል ብለዋል። በ2012 ዓ.ም በጀት ዓመት አጋማሽ ከበይነ መንግስታዊ ተቋማትና ከመንግስታት ሁለትዮሽ ትብብር ምንጮች 39 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር በላይ በብድርና እርዳታ መልክ ቃል ተገብቷል። ከምንጮች ቃል ከተገባው ገንዘብ ፈሰስ ተደርጎ ለፕሮጀክቶችና ፕሮግራሞች ማስፈፀሚያ እንዲሆን በመንግስት እጅ የገባው  ከ54 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በላይ ነው። ይህም ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ከተመዘገበው የብድርና እርዳታ ፍሰት ጋር ሲነፃፀር ተቀራራቢ መሆኑ ታውቋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም