ነገ ኢትዮጵያ ነዳጅ የማምረት ሙከራ ትጀምራለች-ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ

164
አዲስ አበባ ሰኔ 20/2010 በምስራቅ ኢትዮጵያ ሲካሄድ የነበረው የነዳጅ ፍለጋ ስኬታማ በመሆኑ ከነገ ጀምሮ ኢትዮጵያ ድፍድፍ ነዳጅ የማምረት ሙከራ እንደምትጀምር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ይፋ አደረጉ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዛሬ በሰጡት መግለጫ “ፖሊ ጂሲኤል ፔትሮሊየም ሆልዲንግ” በተሰኘው የቻይና ኩባንያ በሱማሌ ክልል ሲካሄድ በቆየው የነዳጅ ፍለጋ መሰረት “ኢላላ” በተባለ የቁፋሮ ቦታ የተገኘውን ድፍድፍ ነዳጅ የማምረት ሙከራ ይጀምራል። ከተቆፈሩት ስምንት ጉድጓዶች መካከል በሶስቱ ድፍድፍ ነዳጅ መገኘቱን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ነገ ሐሙስ ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የድፍድፍ ነዳጅ ማምረት ሙከራ የምትጀምርበት ዕለት መሆኑን አብስረዋል። የተፈጥሮ ጋዝ ፍለጋም ስኬታማ በመሆኑ ከመጭው መስከረም ጀምሮ በሁለት ዓመታት ውስጥ የሚጠናቀቅ  የነዳጅ ቱቦ ዝርጋታ ወደ ጂቡቲ ይካሄዳል። ነዳጅ በሚወጣበት ስፍራ ያለው የተፈጥሮ ጋዝ ክምችት ከስድስት እስከ ስምንት ትሪሊዮን ኪዩቢክ ፊት እንደሚሆን ተገምቷል፡፡ ኢትዮጵያ የተፈጥሮ ነዳጅ መላክ ስትጀምር በዓመት ከአንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሪ ለማግኘት ያስችላታል ተብሏል። በአገሪቷ ነዳጅ መገኘቱ ለውጭ ምንዛሪ ግኝትና ለስራ ዕድል ፈጠራ የሚኖረው ኢኮኖሚያዊ ፋይዳው ከፍተኛ ቢሆንም ሌሎች ሁለንተናዊ የልማት ስራዎች ግን ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አረጋግጠዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም