የጎልማሶች ትምህርት የመቆም ስጋት ተጋርጦበታል

82

ወልዲያ የካቲት 11/2012 (ኢዜአ) በሰሜን ወሎ ዞን የተቀናጀ የጎልማሶች ትምህርት በቅንጅት መጓደልና በበጀት እጥረት ምክንያት ሙሉ በሙሉ ለመዘጋት መቃረቡን የዞኑ ትምህርት መምሪያ አስታወቀ።

በመምሪያው የጎልማሶችና የማህበረሰብ ልማት ባለሙያ አቶ ደሳለኝ አስፋው ለኢዜአ እንደገለፁት የተቀናጀ የጎልማሶች ትምህርት ለሁለንተናዊ እድገት ወሳኝ ቢሆንም በዞኑ በሚፈለገው አግባብ እየሄደ አይደለም።

የጎልማሶች ትምህርት በጤና፣ በግብርና ፣ በትምህርት ፣ በጥቃቅንና አነስተኛና በመሰል ተቋማት ቅንጅት የሚመራ መሆኑን ገልፀዋል።

ይሁን እንጂ በየጊዜው እየተገናኙ በመገምገምና አቅጣጫ አስቀምጦ በመስራት በኩል ሰፊ ክፍተት በመኖሩ አሁን ላይ የመማር ማስተማር ስራው በእጅጉ ተዳክሟል።

በዚህ በጀት ዓመት በ1ኛ እና 2ኛ ደረጃ የጎልማሶች ትምህርት 157 ሺህ የሚጠጉ ጎልማሶችን መዝግቦ ለማስተማር ታቅዶ አንደ ነበር አስታውሰዋል።

ከታቀደው ውስጥ 99 ሺህ ምዝገባ ተካሔዷል ቢባልም አሁን ላይ በተቆራረጠ አግባብ  በትምህርት የሚገኙት 730 ጎልማሶች ብቻ በመሆኑ ሁኔታው አሳሳቢ እንዳደረገው  አብራርተዋል።

ተማሪዎች ይማሩበታል የተባሉትን ጣቢያዎች ለመጎብኘት ሙከራ ቢደረግም ተማሪዎቹ አለመገኘታቸውን ባለሙያው ተናግረዋል፡፡

ለዚህም ባለድርሻ አካላት ተቀናጅቶ አለመስራት መሆኑን ጠቅሰው  ከዚህ በፊት ለአመቻቾች በየወሩ ይከፈል የነበረው 500 ብር በክልሉ መንግስት መከልከሉ ደግሞ ችግሩን እንዳባባሰው ገልፀዋል።

የዞኑ ጤና መምሪያ ሃላፊ ወይዘሮ ሰላማዊት አያሌው በበኩላቸው የጎልማሶችን ትምህርት በበላይነት መምራት ያለበት የትምህርት ዘርፉ ነው።

የጎልማሶች ትምህርት የሁሉም ባለድርሻ አካላት ተሳትፎ የሚጠይቅ ቢሆንም የትምህርት ዘርፉ የሚያስፈልጉ ባለሙያዎችን በመጠየቅ እንዲመደቡለት መጠየቅ ሲገባው ማድረግ አልቻለም ብለዋል።

አሁንም ቢሆን ችግሩን ከመግፋት ወጥቶ በጋራ በመገምገም አስተካክሎ ማስቀጠል ይገባል ሲሉ ገልፀዋል።

የሰሜን ወሎ ዞን ምክትል አስተዳዳሪና የግብርና መምሪያ ሃላፊ ዲያቆን ተስፋሁን ባታብል በበኩላቸው የጎልማሶች ትምህርት ዋና ባለቤቱ የትምህርት ሴክተሩ ሆኖ እያለ በባለቤትነት አልመራውም ብለዋል፡፡

ችግሮቹን ለቦርድና ለሴክተር መስሪያ ቤቶች አቅርቦ ማስገምገም እንደነበረበትና ይህንን ባለመፈፀሙ ዘርፉን እንደጎዳው አስረድተዋል ።

አሁን በተዳከመ መንገድ የሚስተዋለውን የጎልማሶች ትምህርት አፈፃፀም በቅርቡ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመገምገም ችግሩን ለመፍታት ይሰራል ብለዋል ።

የዞኑ ትምህርት መምሪያ ለቀረበበት ወቀሳ በሰጠው ምላሽ በዓመቱ መጀመሪያ እቅዱን በቦርድ እንዲታይ አድርጎ ወደ ስራ መግባቱን በመግለፅ አሁን ላጋጠመው ችግር ሁሉንም በየደረጃው የሚጠየቅበትና ኃላፊነት የሚወስድበት እንጂ ወደ አንድ ወገን የሚወረወር አይደለም ብሏል ።

በሰሜን ወሎ ዞን በ2004 ዓ.ም የተጀመረው የጎልማሶች ትምህርት እስከ አሁን ድረስ በተለያዩ ደረጃዎች ከ100 ሺህ የሚበልጡ ጎልማሶችን ማስተማር እንደተቻለ መረጃዎች ያመላክታሉ ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም