በትግራይ 160 አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የድጂታል ትምህርት ፕሮግራም ተጠቃሚ ሆኑ

67
መቀሌ ኢዜአ የካቲት11/2012 ዓ/ም የትግራይ ልማት ማህበር/ትልማ/ በክልሉ የሚገኙ 160 አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን የዲጂታል ትምህርት ፕሮግራም ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማድረጉን አስታወቀ። የልማት ማህበሩ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ አስተባበሪ አቶ ንጉሰ ገብረክርስቶስ ለኢዜአ እንደገለፁት   በክልሉ በመሰጠት ባለው የገመድ አልባ (ዋይፋይ) የመማር ማስተማር ስራ ተማሪዎች የትምህርት ፍላጎታቸውን እንዲጨምር አስችሏል ። በታብሌት ሞባይልና ላፕቶች በመታገዝ እየተሰጠ ባለው የትምህርት ፕሮግራም የአምስተኛ ክፍል ተማሪዎች በእንግሊዝኛ ቋንቋ የመናገርና የመጻፍ ችሎታቸውን እንዲዳብር እንዳደረገው አስተባባሪው ገልፀዋል ። ባለፈው የትምህርት ዘመን በ40 ትምህርት ቤቶችና በ7 ሺህ 200 የአምስተኛ ክፍል ተማሪዎች በሙከራ ደረጃ የተጀመረው ይኸው ፕሮግራም ውጤት በማምጣቱ ዘንድሮ ወደ 160 ትምህርት ቤቶች ማስፋት መቻሉን አስረድተዋል ። በወረቀት አልባ ከሚሰጡ የትምህርት ፕሮግራሞች መካከልም እንግሊዝኛ ፣ ሂሳብ፣ ሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ የትምህርት ዓይነቶች ይገኙባቸዋል። ፕሮግራሙ ከመጀመሩ በፊት መደበኛ ትምህርታቸውን የሚያቋርጡ የአምስተኛ ክፍል ተማሪዎች ቁጥር በርካታ ነበር ብለዋል። በአጠቃላይ በፅሁፍና በቪድዮ እየተዘጋጀ በታብሌት ሞባይል ለሚሰጣቸው ትምህርትና የብቃት መለኪያ ፈተና  በንቃት የመከታተልና የማለፍ ብቃታቸውን እንደጨመረላቸው ነው አስተባባሪው ያስታወቁት። በትምህርት ቤቶቹ የሚገኙ 28 ሺህ 800 የአምስተኛ ክፍል ተማሪዎች የድጂታላይዜሽን ትምህርት በመከታተል ላይ ይገኛሉ ብለዋል ። የትግራይ ልማት ማህበር የጀመረው የዲጂታላይዜሽን ትምህርት ፕሮግራም ተማሪዎች ወደ ዘጠነኛ ከፍል ሲሻገሩ ለቴክኖሎጂ ቅርበት እንዲኖራቸው በማድረግ ትምህርታቸውን በብቃት ለመከታተል እንደሚያግዛቸው አቶ ንጉሰ ተናግዋል። የትምህርት ፕሮግራሙን ለማስፋትና በክልሉ ወደ የሚገኙ 2 ሺህ 400 ትምህርት ቤቶች ለማድረስ የረጅም ጊዜ እቅድ ተይዞ እየተሰራበት መሆኑንም አስታውቀዋል። በትምህርት ቤቶች ውስጥ ከ360 ሺህ በላይ ተማሪዎችን ተጠቃሚ ለማድረግ ያለመ መሆኑንም ተናግረዋል። በትግራይ የጥራት ደረጃው የጠበቀ ትምህርት የቀሰመ ትውልድን ለማፍራት የተጀመረው ጥረት ከግብ ለማድረስ የሚያገለግሉ የኤልክትሮኒክስ ፣ የገንዘብና የሙያተኞች ድጋፍ ፕሮፍችሮ/profuturo/ፋውንደሽን የተባለ የስፔን ምግባረ ሰናይ ድርጅት እገዛ እያደረገ መሆኑን አቶ ንጉሰ ገልፀዋል። ምግባረ ሰናይ ድርጅቱ እስከ አሁን ድረስ ከ46 ሚሊዮን ብር የሚበልጥ ጥሬ ገንዘብና የኤሌክትሮኒክ ቁሳቁሶች ድጋፍ ማድረጉን አመልክተዋል። የተጀመረው የወረቀት አልባ ትምህርት ፕሮግራም ውጤታማ ከሆነ ለቀጣይ ዓመታት ተጨማሪ ከ39 ሚልዮን ብር በላይ ለመስጠት ቃል መግባቱንም አስታወቀዋል። የድጂታላይዜሽን ትምህርት ተጠቃሚ ከሆኑ ተማሪዎች መካከል በመቀሌ ከተማ የኢትዮ -ቻይና   አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ ቤተልሄም ወልዳይ እንዳለችው  በታብሌት ሞባይል አጠቃቀም ለ14 ቀናት የወሰደችውን ስልጠና በአግባቡ እየተገለገለችበት መሆኑን ተናግራለች። ''ፕሮግራሙ ትምህርቴን በንቃት እንድትከታተልና በፈተና ወቅትም ጥሩ ውጤት በማምጣት ሁለተኛ እና ሦስተኛ ደረጃን በመያዝ እንዳጠናቅቅ አግዞኛል ብላለች።'' የፕሮግራሙ ተጠቃሚ ተማሪ ዳግም ዳኘ በበኩሉ በቪድዮና በፅሁፍ እየታገዘ እየተሰጠን ባለው የመማር ማስተማር ፕሮግራም በእንግሊዝኛና በሂሳብ የነበረኝን ዝቅተኛ ውጤት እንዳሻሽልና ከጎበዝ ተማሪዎች ተርታ እንድሰለፍ አድርጎኛል ብሏል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም