በደብረብርሃን የመሮጫ መም ግንባታ በመቋረጡ መቸገራቸውን አትሌቶች ገለጹ

92
ደብረ ብርሃን የካቲት 10/2012  ከሁለት ዓመት በፊት የተጀመረው የመሮጫ መም ግንባታ መቋረጡ ችግር እንደፈጠረባቸው የደብረብርሃን አትሌትክስ ማሰልጠኛ ማእከል ሰልጣኞች ገለፁ ። ችግሩ የተፈጠረው በሁለት ነጥብ አምስት ሚሊየን ብር ወጪ ከሁለት ዓመት በፊት ግንባታው የተጀመረው የመሮጫ  መም በዲዛይን ለውጥ ምክንያት በመቋረጡ የተፈጠረ ነው ተብሏል ። በማዕከሉ በመሰልጠን ላይ የምትገኘው ወጣት ብዙነሽ ጌታሁን ለኢዜአ እንደገለጸችው  ማዕከሉ በዓለምና በአፍሪካ የወጣቶች ሻምፒዮናና በሌሎች ስፖርታዊ ውድድሮች  አሸናፊ የሆኑ አትሌቶችን እያፈራ ይገኛል። በአትሌትክስ ማእከሉ የመሮጫ መም ቢገነባለት ከዚህ በላይ ውጤቶችን ማስመዝገብ የሚችሉ አትሌቶችን በብዛት ማፍራት ይቻል ነበር ብላለች። የአካባቢው የመሮጫ መም ችግር ለመፍታት የዛሬ ሁለት ዓመት የተጀመረው ግንባታ ባላወቁት ምክንያት በመቋረጡ ተስፋ እንዳስቆረጣቸው ተናግራለች። አትሌት አድሴ ዓለሙ በበኩሏ ማዕከሉ የመሮጫ መም፣ የመዝናኛ ክበብ፣ የመጸዳጃ ቤት፣ የአምቡላንስና ሌሎች ችግሮች አሉበት ። ውድድር ሲኖር በደብረ ብርሃን መምህራን ማሰልጠኛ ኮሌጅና 20 ኪሎ ሜትር ርቀት ወደ ሚገኘው ጫጫ ከተማ በግል ወጪያቸው በመሔድ ልምምድ እየሰሩ እንደሚገኙ ገልጻለች። የማሰልጠኛ ማእከሉ ዋና አሰልጣኝ አቶ አማረ ሙጨ እንደገለጹት የአትሌቲክስ ማእከሉ የአገራችን ስም የሚያስጠሩ አትሌቶች በማፍራት ላይ ይገኛል ። ማዕከሉ የበጀትና የቁሳቁስ ችግሮች ስላሉበት ዘንድሮ መቀበል የነበረበት ከ50 በላይ አትሌቶችን ለመቀበልና  የሶስት አሰልጣኞች ቅጥር ለመፈፀም የያዘውን እቅድ ማሳካት አለመቻሉን ተናግረዋል፡፡ የሰሜን ሸዋ ዞን ስፖርት ኮሚሽን ሀላፊ አቶ ክላል ሳህለማሪያም ስለጉዳዩ ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ ችግሩ በዞኑ መስተዳድር የሚታወቅ ቢሆንም ፈጥኖ በማስተካከል በኩል ውሱንነት ነበር። መፀዳጃና ጅምናዚየም በመገንባት ችግሩን ለማቃለል መንግስት 700 ሺህ ብር ተመድቦ እንቅስቃሴ መጀመሩን አስረድተዋል ። በአሁኑ ወቅትም ከዞኑና ከክልሉ መስተዳድር ጋር በመተባበር የተቋረጠውን የመሮጫ መም እንደገና ለማስጀመር እየተሰራ ነው። የአትሌቲክስ ማዕከሉ እስከ አሁን 140 ወጣቶችን አሰልጥኖ ለተለያዩ ክለቦች በማስረከብ ለቁም ነገር ያበቃ ነው ተብሏል ።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም