የአርባምንጭ ዩኒቨርሲቲ ለአጠቃላይ ሆስፒታሉ የገንዘብና የህክምና ቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ

67

አርባ ምንጭ የካቲት 11/2012 (ኢዜአ) የአርባምንጭ ዩኒቨርሲቲ በከተማው ለሚገኘው አጠቃላይ ሆስፒታል የገንዘብና የህክምና ቁሳቁስ ድጋፍ ማድረጉን ገለፀ። የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ዳምጠው ዳርዛ ለኢዜአ እንደገለጹት ሆስፒታሉ ከህክምና አገልግሎት ጎን ለጎን በማስተማሪያ ዙሪያም ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በሆስፒታሉ ላይ ያለውን የሥራ ጫና በተወሰነ ደረጃ ለማቃለል እንዲረዳ ለመድሃኒት ግዥ የሚያገለግል አንድ ሚሊዮን ብር ጥሬ ገንዘብና 700 ሺህ ብር ግምት ያላቸው የአጥንት ህክምና ቁሳቁስ ድጋፍ አድርጓል፡፡

በቀጣይም ዩኒቨርሲቲው ከአርባ ምንጭ አጠቃላይ ሆስፒታል ጋር አብሮ እንደሚሰራ ዶክተር ዳምጠው አረጋግጠዋል፡፡

የአርባ ምንጭ አጠቃላይ ሆስፒታል ስራ አስኪያጅ አቶ ተመስገን ተሾመ በበኩላቸው ሆስፒታሉ በዓመት ከ5 ሚሊዮን በላይ የጋሞ ፣ ጎፋና በዙሪያው የሚገኙ ዞኖች የሚያስተናግድ በመሆኑ በአገልግሎት አሰጣጡ ሒደት ጫናው ከፍተኛ መሆኑን ገልፀዋል ።

ለአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲና ለአርባ ምንጭ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ህክምና ተማሪዎች ላለፉት ዘጠኝ ዓመታትየተግባር ላይ ትምህርት መስጫ ሆኖ ሲያገለግል መቆየቱንም አስረድተዋል ።

ዩኒቨርሲቲው ያደረገው ድጋፍ በሆስፒታሉ የነበረውን የመድሃኒትና የአጥንት ህክምና መገልገያ መሣሪያዎች እጥረት በመጠኑ ሊቀንስ እንደሚችልና ለከተማዋና አካባቢው የሚኖረው ፋይዳ ከፍተኛ መሆኑን ጠቁመው ድጋፉ ተጠናክሮ ይቀጥላል የሚል ተስፋ እንዳላቸው ተናግረዋል ።

ሆስፒታሉ በተሽከርካሪና በተለያዩ ድንገተኛ አደጋዎች ተጎድተው የሚመጡ በርካታ ህሙማን እንደሚያስተናግድ የጠቆሙት ደግሞ የአጥንት ህክምና ክፍል አስተባባሪ ሲስተር የትናየት ወንድማገኝ ናቸው፡፡

ዩኒቨርሲቲው ያደረገልን የአጥንት ህክምና ቁሳቁሶች በመሣሪያ እጥረት ምክንያት ተጎጂዎች ወደ ወላይታ ክርስቲያን ሆስፒታል እንዲላኩ ሲያደርግ የነበረውን አስገዳጅ ሁኔታ እንደሚያቃልለው ገልፀዋል ።

በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የ6ኛ ዓመት የህክምና ተማሪ ከበደ አልማው እንዳለው አርባ ምንጭ አጠቃላይ ሆስፒታል ለህክምና ተማሪዎች የተግባር ትምህርት የሚሰጥበት በመሆኑ በቁሳቁስ መሟላቱ በቂ ዕውቀት እንድናገኝ ያግዛል ብሏል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም