የኢትዮጵያ ተማሪዎች ህብረት ኮንፈረንስ በኢስታንቡል ተካሄደ

63
የካቲት 11/2012 (ኢዜአ) በቱርክ የኢትዮጵያ ተማሪዎች ህብረት 14ኛው ጉባኤ በኢስታንቡል ተካሄደ። በቱርክ የኢትዮጵያ ተማሪዎች ህብረት 14ኛው ጉባኤ ከየካቲት 6 እስከ 8 ቀን 2012 ዓ.ም በኢስታንቡል ተካሂዷል። በጉባኤው ላይ የተገኙት በቱርክ የኢፌዲሪ አምባሳደር ግርማ ተመስገን ባደረጉት ንግግር ኢትዮጵያ አሁን ላይ በብሩህ የተስፋ ምዕራፍ ላይ እንደምትገኝ ገልጸዋል። ሆኖም በሽግግር ሂደቱ ሁሉም ነገር አልጋ በአልጋ ባለመሆኑ ሊታለፉ የሚችሉ የተለያዩ ፈተናዎች መኖራቸውንም ጠቁመዋል። የሚከሰቱ ፈተናዎችን ለመወጣት ኢትዮጵያዊያን በያሉበት በአንድነት በጎ አስተዋጽኦ የማበርከትና የአገሪቷን ህዳሴ እውን የማድረግ ርብርቦሽ እንዲያደርጉም ጠይቀዋል። በቱርክ ትምህርታቸውን አጠናቀው በቅርቡ ወደ ሀገራቸው የሚመለሱ ተማሪዎች የቀሰሙትን እውቀትና ክህሎት ወደ ተግባር በመተርጎም አገራቸውን ማገልገል እንዳለባቸውም አሳስበዋል። በኢትዮጵያ እየተካሄደ ባለውየለውጥና የብልጽግና ሂደት ውስጥ በጎ አሻራቸውን እንዲያሳርፉም በኮንፈረንሱ ላይ መልክታቸውን አስተላለፈዋል። በመድረኩ ላይ የኢትዮጵያን ተጨባጭ ሁኔታ በሚመለከት የተለያዩ ሃሳቦች ተነስትው ውይይት ተደርጎባቸዋል። በቱርክ በትምህርት ዘመኑ በተለያዩ የትምህርት ዘርፎች ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገቡ ተማሪዎችም በእለቱ የእውቅና ሽልማት ተበርክቶላቸዋል፡፡ መድረኩ ላይ ከ200 በላይ በቱርክ ልዩ ልዩ ዩኒቨርስቲዎች የሚማሩ ተማሪዎች፤ የተለያዩ የቱርክ ባለስልጣናትና ኩባንያዎች ተገኝተዋል፡፡ መድረኩ በቱርክ የኢትዮጵያ ኤምባሲ፤ የኢትዮጵያና ቱርክ ፓርላማ ወዳጅነት ኮሚቴ፤ በቱርክ የኢትዮጵያ ተማሪዎች ማህበር አመራር አባላት በቅንጅት የተዘጋጀ መሆኑን የኢፌዲሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ፅህፈት ቤት መረጃ ያመለክታል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም