ለውጡን ተከትሎ የተከሰቱ ችግሮች ምንጩ የዴሞክራሲ ባሕል አለመዳበር ነው

113

አዲስ አበባ፤ የካቲት 10/2012(ኢዜአ) በኢትዮጵያ የመጣውን ለውጥ ተከትሎ የሚታዩ ችግሮች ምንጫቸው በአገሪቷ የዴሞክራሲ ባሕል አለመዳበር ነው ሲሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ተናገሩ።

መንግስት በአገሪቷ የሚታዩ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ችግሮችን ለመፍታት ባደረገው ጥረት ችግሮቹ እየቀነሱ ቢሆንም አሁንም ቀሪ ስራዎች ይጠብቁናል ሲሉም ተናግረዋል።

ሚኒስትሩ በኢትዮጵያ ይፋዊ ጉብኝት በማድረግ ላይ ካሉት የአሜሪካ አቻቸው ማይክል ፖምፒዮ ጋር የጋራ መግለጫ ሰጥተዋል።

ባለስልጣናቱ ሁለቱ አገራት በውስጣዊ አገራዊ ጉዳዮች፣ በምስራቅ አፍሪካ፣ ዓለም አቀፍ ፖለቲካዊና ዲፕሎማሲያዊ ትብብሮቻቸውን በሚያሳድጉበት ሁኔታ ላይም መክረዋል።

አቶ ገዱ ኢትዮጵያ እየገነባችው ስላለው አዲስ የለውጥ ሂደት በሰጡት ማብራሪያ ለውጡን ተከትሎ የሚታዩ የህግ የበላይነት አለመከበርና ተያያዥ ጉዳዮች የመነጩት በአገሪቷ የዴሞክራሲ ልምምድ ባለመዳበሩ ነው ብለዋል።

በተለይ በፖለቲካና በመገናኛ ብዙሃን መስኮች መንግስት ሰፊ ነፃነት ከመስጠቱ ጋር ተያይዞ እየተፈጠሩ የነበሩ ግጭቶችና አለመግባባቶች እንደ አንድ የለውጡ ፈተና አይተናቸዋል ብለዋል።

"እነዚህን ችገሮች ለመፍታት እየሰራን ነው" ያሉት አቶ ገዱ መንግስት ችግሮቹን ለመፍታት ባደረገው ጥረት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተቃለሉ መምጣታቸውንም አክለዋል።

የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማይክ ፖምፒዮ በበኩላቸው በኢትዮጵያ ጉብኝታቸው የሁለቱን አገራት ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የሚያጠናክሩ ጉዳዮች ምክክሮችን ማድረጋቸውን ገልፀዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካና በሌሎች አካባቢዎች ሠላም ለማስፈን በተለያዩ ዓለምና አህጉር አቀፍ ድርጅቶች ስር የምታደርገውን ተሳትፎም አድንቀዋል።

ከዚህ ጋር አያይዘውም በተለይም በኢትዮጵያ የመጣው ለውጥ የሁለቱን አገራት ኢንቨስትመንት፣ የንግድና የዲፕሎማሲ ግንኙነት የበለጠ ለማጠናከር ምቹ ሁኔታን የፈጠረ ነው ሲሉም ተናግረዋል።

ለውጡን ተከትሎ በኢትዮጵያ ኢንቨስት ለማድረግ የሚመጡ የአሜሪካ ባለሃብቶች ቁጥር እየጨመረ መሆኑንና ይህም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።

አሜሪካ ኢትዮጵያ የጀመረችው ለውጥ ከዳር እንዲደርስ ድጋፍ እንደምታደርግም ተናግረው፤ አገራቸው በምስራቅ አፍሪካ የተከሰተውን አንበጣ ለመከላከል የሚውል 8 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ ማድረጓንም ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም