ለሰላማዊ የትምህርት ስራ መጠናከር እንደሚጥሩ የደብረብርሀን ዩኒቨርሲቲ መምህራን ገለጹ

72

ደብረብርሃን ኢዜአ የካቲት 10/ 2012 ፡- ዘላቂ የሆነ ሰላማዊ የመማር ማስተማር ስራ ተጠናክሮ እንዲቀጥል የሚጥሩ መሆናቸውን የደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ መምህራን ገለፁ። የዩኒቨርስቲ የግማሽ በጀት ዓመት የእቅድ አፈፃፀምና ቀጣይ የመማር ማስተማር ስራዎች ዙሪያ ውይይት ተካሄዷል።

በውይይቱ ወቅት የስነ-ባህሪይ መምህር ፍቃዱ ገበየሁ  እንዳሉት ተማሪዎች  እውቀት ከመገብየት ባለፈ በስነ ምግባር የታነፁ መሆን ይኖርባቸዋል።

በስነ ምግባር የታነፀና የወደፊት ዓላማው እንዲሳካ ዛሬ ላይ በትምህርት ውጤታማ የሆኑ ተማሪዎችን ለማፍራት በትብብር መስራት የግድ መሆኑን ተናግረዋል።

በተለይም ዘላቂ የሆነ ሰላማዊ የመማር ማስተማር ስራ እንዲጠናከር የተማሪዎች ስነ ምግባር ላይ በትኩረት መስራት ያስፈልጋል።

በዩኒቨርሲቲው የመጀመሪያ መንፈቅ ዓመት የታየው የተሻለ የመማር ማስተማር ስራ በቀጣየም  ተጠናክሮ እንዲቀጥል  የበኩላቸውን ለመወጣት እንደሚጥሩ ገልጸዋል።

የጋዜጠኝነት ትምህርት ክፍል ኃላፊ መምህር ዘሪሁን ኃይሉ በበኩላቸው  ተማሪዎች በማህበራዊ ሚዲያዎች ለሚናፈሱ ወሬዎች ትኩረት ሊሰጡ እንደማይገባ ተናግረዋል።

"የተማሪዎች የመጀመሪያ ሚና በትምህርታቸው ውጤታማ እንዲሆኑ ሳይሰለቹ መትጋትና ብቁ ተወዳዳሪ ሆነው መገኘት ነው "ብለዋል።

ተማሪዎች በምክንያት የሚያምኑና በትክክለኛ መረጃ የበለፀጉ እንዲሆኑ በማድረግ ሰላማዊ የመማር ማስተማር እንዲሰፍን በሙያቸው የድርሻቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል።

በተቋሙ  ዘላቂ የሆነ ሰላማዊ የመማር ማስተማር ስራ በማጠናከር ተማሪዎቻቸውን ለማብቃት እንደሚጥሩ መምህራኑ በሰጡት አስተያየት ገልጸዋል።

የዩኒቨርሲቲዉ ፕሬዚዳንት ዶክተር ንጉስ ታደሰ  በተቋሙ በመጀመሪያው መንፈቅ ዓመት ለሰላማዊ የመማር ማስተማር ስራው ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ በመሰራቱ የከፋ ችግር ሳያጋጥም መጠናቀቁን አስረድተዋል።

ሰላማዊ የመማር ማስተማር ስራውን ዘላቂ ለማድረግም በጥናትና ምርምር የታገዘ የሰላም መፍትሄ ሃሳብ ቀርቦ እየተሰራበት መሆኑን አመልክተዋል።

"በዩኒቨርሲቲው አንድ ተማሪ በትምህርቱ ውጤት ለማስመዝገብ በሚያደርገው ጥረት ልክ በስነ ምግባሩም የታነፀ እንዲሆን እየተሰራ ነው "ብለዋል።

ይህን ለመደገፍና ለማገዝም የተማሪዎች ስነ ምግባርና ስብእና ግንባታ ዳይሪክቶሬት መቋቋሙን ጠቅሰዋል።

ባለፈው ጊዜ ተፈጥሮ በነበረው መጠነኛ ችግር ተሳታፊ የነበሩ መምህራን፣ የአስተዳደር ሰራተኞችና በዩኒቨርስቲው  በጥቃቅና አነስተኛ ማህበራት የተደራጁ ግለሰቦች ላይ እርምጃ በመውሰድ ማስተካከል እንደተቻለም አስረድተዋል ፡፡

በደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ በሁሉም የትምህርት መርሃ ግብሮች 27 ሺህ 600 ተማሪዎች በትምህርት ላይ እንደሚገኙም ተመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም