የደቡብ ሱዳን የአስተዳደር ግዛቶች ወደ 10 ዝቅ ማለታቸው በአገሪቷ ሠላም ሊያመጣ ይችላል

99
የካቲት 10/2012(ኢዜአ) የደቡብ ሱዳን ገዥ ፓርቲ የአገሪቷን የአስተዳደር ግዛቶች ከ32 ወደ 10 ዝቅ ለማድረግ ያቀረበው የውሳኔ ሃሳብ ሠላም ሊያሰፍን እንደሚችል ተገለጸ። በደቡብ ሱዳን ዓመታትን ያስቆጠረው ደም አፋሳሽ የእርስ በእርስ ግጭት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎችን ለስደት፤ ሺህዎችን ደግሞ ለሞት መዳረጉ ይታወቃል። በገዥው ፓርቲ መሪ ሳልቫ ኪር ማያርዲትና በተቀናቃኛቸው ዶክተር ሪክ ማቻር መካከል ባለው አለመግባባት ደቡብ ሱዳናዊያን ዛሬም የሠላም አየር እንደራቃቸው ናቸው። በዱቡብ ሱዳን ሰማይ ስር ሠላም ለማስፈን በፕሬዚደንት ሳልቫ ኪርና በቀድሞ ምክትል ፕሬዚዳንታቸው ዶክተር ሪክ ማቻር መካከል ከ16 ጊዜ በላይ የተደረጉ የሠላም ስምምነቶችም ተግባራዊ አልሆኑም። መረጃዎች እንደሚያሳዩት ጠዋት የተስማሙበትን ከሠዓት በኋላ በሚያፈርሱት ሁለቱ ተቀናቃኝ ኃይሎች ምክንያት በደቡብ ሱዳን ሠላም ከራቀ ከሰባት ዓመት በላይ ተቆጥሯል። በዜጎች ላይ የማያባራውን እንግልት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ በማስቆም ወደ ሠላም ለመመለስ የገዥው ፓርቲ የአገሪቷን የአስተዳደር ወሰን የመቀነስን ሃሳብ አቅርቧል። የፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር አስተዳደር በአገሪቷ የአስተዳደር ግዛቶች ላይ ለማድረግ ያሰበውን ማሻሻያ አስመልክቶ በኢትዮጵያ የደቡብ ሱዳን አምባሳደር ዛሬ መግለጫ ሰጥተዋል። አምባሳደሩ ጀምስ ሞርጋን በአዲስ አበባ በሰጡት መግለጫ እንዳሉት በአገሪቷ ለዓመታት የዘለቀውን የእርስ በእርስ ግጭት ለማስቆም የፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር አስተዳደር የአስተዳደር ግዛቶችን የመቀነስ የመፍትሄ ሃሳብ አቅርቧል። 32 የደቡብ ሱዳን የአስተዳደር ግዛቶችን ወደ 10 ዝቅ ማድረግ የሚያስችለው የውሳኔ ሃሳብ ባለፈው ዓርብ የካቲት 6 ቀን 2012 ዓ.ም መቅረቡን ነው የገለጹት። የነዳጅ ክምችት ማዕከል እንደሆነች የሚነገርላት የ"ሩወንግ" ግዛት፣ አብዬና ግሬት ፒቦር ግዛቶች ባሉበት እንደሚቀጥሉም አመልክተዋል። የአንድነት የሽግግር መንግስት በምርጫ እስከሚመሰረት ድረስ ሦስቱ የአስተዳደር ግዛቶች በፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር አስተዳደር ስር እንደሚቆዩም ገልጸዋል። የሳልቫ ኪር አስተዳደር ከተቀናቃኙ ጋር ያለውን አለመግባባት በሠላማዊ መንገድ ለመፍታት የመነጨ ሳሃብ መሆኑንም አምባሳደሩ ጠቁመዋል። "የደቡብ ሱዳን የሠላም እጦት ከዚህ ቀደም በተፈጠሩ የእርስ በእርስ ግጭቶች በሞቱ፣ በቆሰሉ፣ ከመኖሪያ ቀዬአቸው በተፈናቀሉ ዜጎች መቆም ይኖርበታል" ሲሉም ተናግረዋል። በሁለቱ ተቀናቃኝ ኃይሎች መካከል የሚደረገው ስምምነት ተግባራዊ ከሆነ ከደቡብ ሱዳን የተሰደዱ ዜጎችን መልሶ ማቋቋም፣ መሠረተ ልማት መገንባትና ምርጫ ማካሄድ የመንግስት ቀዳሚ ሥራ እንደሚሆን አመልክተዋል። የፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር ማያርዲት አስተዳደር ያቀረበው ሃሳብ በተቀናቃኛቸው ዶክተር ሪክ ማቻር ተቀባይነት ስለማግኘቱ ግን የታወቀ ነገር የለም።        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም