የአፍሪካ የምድር ጦር ኃይሎች ጉባዔ እየተካሄደ ነው

88

የካቲት 10/2012 ዓ.ም ስምንተኛው የአፍሪካ የምድር ጦር ኃይሎች ጉባዔ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው ። ጉባዔው በአፍሪካ በሚገኘው የአሜሪካ ጦርና በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ትብብር የተዘጋጀ ነው።

የመጀመሪያው የአፍሪካ የምድር ጦር ኃይሎች ጉባዔ በአውሮፓዊያኑ የዘመን አቆጣጠር 2010 በዋሽንግተን ዲሲ ነበር የተካሄደው።

ኡጋንዳ፣ ሴኔጋል፣ ታንዛንያ፣ ማላዊ፣ ናይጄሪያ፣ ቦትስዋና በቅደም ተከተል ከሁለተኛ እስከ ሰባተኛ ጉባዔው የተካሄደባቸው አገራት ናቸው።

የዘንድሮው ጉባዔ "ለነገ ደህንነት ፍላጎት የዛሬ አመራር" በሚል መሪ ሃሳብ እየተካሔደ ነው።

ለአራት ቀናት በሚዘልቀው በዚህ ጉባዔ በወታደራዊ የአመራር ልማት ላይ የልምድ ልውውጥ እንደሚደረግ ተገልጿል።

የ21ኛው ክፍለ ዘመን የወታደራዊ አመራር ተግዳሮቶች፣ በመከላከያ ተቋማት የአመራር ልማትና በችግር ጊዜ የአመራር ምላሽ የመስጠት አቅም በሚሉ ጉዳዮች ላይም ውይይቶች ይካሄዳሉ ተብሏል።

ከ40 በላይ የአፍሪካ አገራት ወታደራዊ አዛዦች የተሳተፉበት ጉባዔው የአፍሪካና የአሜሪካ የምድር ጦር ኃይሎች ወታደራዊ አዛዦች ሀሳብ የሚለዋወጡበት፣ የጋራ ችግሮቻቸውን በትብብር መፍታት የሚያስችል ግንኙነት የሚመሰርቱበት እንደሆነም ተገልጿል።

በጉባዔው መክፍቻ ላይ የኢፌዴሪ የጦር ኃይሎች ኢታማዦር ሹም ጄኔራል አደም መሐመድ ተገኝተው መልዕክት አስተላልፈዋል።

አፍሪካ ከሽብር እንቅስቃሴ፣ ከባህር ላይ ውንብድና ጋር ተያይዞ የኃያላን አገራትን ትኩረት በመሳቧ በርካታ አገራት በአህጉሪቱ የጦር ሰፈር በመገንባት ላይ መሆናቸውን አውስተዋል።

በመሆኑም በአፍሪካ የሚፈጠሩ ችግሮችን ለመፍታት የአፍሪካ የምድር ጦር ኃይሎች ጉባዔ አይነተኛ ሚና እንደሚኖረው ጄኔራሉ ተናግረዋል።

የአሜሪካ ጦር ተወካይ ጄኔራል ሚካኤል ጋሬትስ በበኩላቸው "የዛሬ መሪዎች ጠንክረው በመስራት ነገ ሊከሰቱ የሚችሉ ችግሮችን ለመመከት መዘጋጀት አለባቸው" ብለዋል።

ወታደራዊ መሪዎች በአገርና በቀጣና ደረጃ ሊኖራቸው የሚችለውን ሚና ጠንቅቀው ማወቅ እንዳለባቸው የጠቆሙት ጄኔራሉ ለዚህም አስፈላጊውን የብቃት ዝግጅት ማድረግ እንደሚገባቸው አመልክተዋል።

የአሜሪካ ጦር ለአፍሪካ አቻው በስልጠና፣ በምክርና ተልዕኮዎችን በመደገፍ እያሳየ ያለውን አጋርነት ይበልጡኑ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አስታውቀዋል።

በተያያዘ ዜና በአዲስ አበባ እየተካሄደ ያለውን 8ኛውን የአፍሪካ ምድር ኃይል ጉባዔ በሚመለከት መግለጫ ተሰጥቷል።

በአፍሪካ የአሜሪካ ጦር አዛዥ ሜጀር ጄነራል ሮጀር ክሉተር እንደገለጹት በአህጉሪቷ ለሚስተዋሉ ችግሮች ተቀራርቦ መስራት እንደሚገባና ለዚህም አሜሪካ ድጋፍ እንደምታደርግ አንስተዋል።

የጉባዔው አዘጋጅ ኮሚቴ ሰብሳቢ ብርጋዴር ጄነራል ጥላሁን አሸናፊም መድረኩ በአህጉሪቱ እያደገ የመጣውን ሽብርተኝነት ጨምሮ ሌሎች ተያያዥ ችግሮችን በጋራ መፍታት በሚቻልባቸው መንገዶች ላይ እንደሚመክር ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም